(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 9/2011)የኢትዮጵያ መንግስት ልኡካን ከኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር አመራሮች ጋር አስመራ ላይ ተወያዩ።
ከኦብነግ ጋር በሚደረገው የሰላም ንግግር አካሔድ ላይ መወያየታቸውም ተመልክቷል።
የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሃላፊና የሶማሌ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ/ሶሕዴፓ/ ሊቀመንበር በአቶ አሕመድ ሺዴ የተመራው የኢትዮጵያ መንግስት የልኡካን ቡድን፣ከአድሚራል ወይንም ጄኔራል ሞሐመድ ኦማር ከተመራው የኦነግ ልኡካን ቡድን ጋር የተወያዩት አስመራ ውስጥ መሆኑም ታውቋል።
አስመራ ውስጥ ትላንት በተካሄደው ውይይት በቀጣይ በሚካሄደው የሰላም ድርድር አካሔድ ላይ ሁለቱም ወገኖች ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተመልክቷል።
የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር/ኦብነግ/ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን የሰላም ጥሪ ተከትሎ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ነሃሴ 12/2018 የተኩስ አቁም ስምምነት ያደረገ ሲሆን ልኡካኑንም ወደ ኢትዮጵያ መላኩ ይታወሳል።
አስመራ ላይ ትላንት በተካሄደው ውይይት ከኦብነግ ሊቀመንበር አድሚራል ሞሀመድ ኦማር ከተመራው ልኡክ ጋር ለመወያየት ወደ አስመራ ከተጓዘው የኢትዮጵያ መንግስት ልኡካን ውስጥ በቅርቡ የሶማሌ ክልልን እንዲመሩ የተሾሙት አቶ ሙስጠፋ ሙሐመድ ይገኙበታል።