(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 3/2011) የቀድሞው የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ የኮፊ አናን የቀብር ስነስርአት ዛሬ ተፈጸመ።
የመጀመሪያውና እስካሁንም ብቸኛ ሆነው የተገኙት የመጀመሪያው አፍሪካዊ የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን በጥቂት ቀናት ህመም ሕይወታቸው ያለፈው ከሶስት ሳምንት በፊት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ነሐሴ 18/2018 ነበር።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1997 እስከ 2006 ለ10 አመታት ያህል 7ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ሆነው አገልግለዋል።
በአንድ ወቅት የአለማችን ቁጥር አንድ ዲፕሎማት የነበሩት ጋናዊው ኮፊ አናን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1962 ጀምሮ ለ44 አመታት ያህል በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ በተለያዩ የሃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሚያዚያ 8/1938 በቀድሞዋ ጎልድ ኮስት በአሁኗ ጋና ከመንታ እህታቸው ኢፍዋ ኦናን ጋር የተወለዱት ኮፊ አናን ከፍተኛ ትምህርታቸውን በጋናና በአሜሪካ ተከታትለዋል።
እንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ እንዲሁም የሀገራቸውን ቋንቋ አካን አቀላጥፈው የሚናገሩት ኮፊ አናን የ3 ልጆች አባትም ነበሩ።
እንደ አውሮፓውን አቆጣጠር በ2001 የሰላም የኖቤል ሽልማትም አግኝተዋል።
በከፍተኛ ወታደራዊ ክብር በተከናወነው የኮፊ አናን የቀብር ስነስርአት ላይ የኢትዮጵያው ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመን ጨምሮ የተለያዩ ሃገራት መሪዎች፣እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሪዝና ታዋቂ ግለሰቦች ተገኝተዋል።
የቀድሞው የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሐፊ ኮፊ አናን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ነሐሴ 18/2018 በስዊዘርላንድ በርን ከተማ ከዚህ አለም በሞት መለየታቸው ይታወሳል።