(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 3/2011) በኢትዮጵያ የተገኘውን ለውጥ ዋጋ ከፍለን ያመጣነው እንጂ በርቀት በማሸነፍ የመጣ ለውጥ የለም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ገለጹ።
በውጭ የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ወደ ሐገር ቤት ሲገቡ ሔደን የምንቀበላቸው ሁላችንም አሸናፊ ስለሆንን ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የአሸናፊነት ስነልቡና አቃፊ ነው፣መግፋት ግን ተሸናፊነት ነው ብለዋል ወቅታዊውን የሃገሪቱን ሁኔታ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ።
ይህን በማድረጋችን እኛን እንደተሸናፊ የቆጠሩ ካሉ ተሳስተዋል ሲሉ አብይ አሕመድ አሳስበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጡት መግለጫ እንደ ሃገር የመጣውን ለውጥ አንዳንዶች ወደ ሐገር ቤት ሲገቡ”እኔ ነኝ ያሸነፍኩት፣ እኔ ነኝ ይህን የፈጸምኩት ይላሉ” ብለዋል።
ነገር ግን በርቀት ማሸነፍ የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እኛ ዋጋ ከፍለን ነው ለውጡን ያመጣነው።ከሕዝባችን ጋር ሆነን ነው ይህንን ለውጥ ያመጣነው።
ይህ ለውጥ ደግሞ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ይበቃል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው።
በዚህ ሒደት ማንም ገለልተኛ ኢትዮጵያዊ ሊኖር አይገባም በሚል ጋብዘን ኤርፖርት ድረስ ሔደን በመቀበል ላይ እንገኛለን ብለዋል።
ከተሰባሰብን ሃይል እንሆናለን፣መበተን ግን ትርፉ ልመና ነው ሲሉም አሳሰበዋል።
በመናቆር የሚገኝ ውጤት እንደ ደቡብ ሱዳንና ሶማሊያ መሆን ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ።
ከኢትዮጵያ ባሻገር ከአካባቢው ሃገራት ጋር በአንድነት በመደመር በአለም ላይ ተጽእኖ ፈጣሪ መሆን እንደሚቻልም አስገንዝበዋል።
በደቡብ ሱዳን መንግስትና ተቀናቃኝ ፓርቲዎች መካከል አዲስ አባባ ላይ በኢጋድ አማካኝነት የተደረሰውን የሰላም ስምምነት በተመለከተም ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ጭምር የዳሰሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ከባንዲራ ጋር ተያይዞ ከሰሞኑ የተፈጠረውንም ውዝግብ ተመልክቷል።
ሁሉም የፈለገውን አርማ ማውለብለብ መብቱ ነው ያሉት ዶክተር አብይ አሕመድ የኢትዮጵያን ባንዲራ መቀየር የሚቻለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲስማማበት ብቻ እንደሆነ አስገንዝበዋል።
በዚህ ሳቢያ መለያየት እንዲመጣ የሚፈልጉ ሃይሎች እንዳሉ ሕዝቡ እንዲገነዘብም አሳስበዋል።
ከለውጡ ጋር ተያይዞ በሩ ሲከፈት የከረፋ ነገር እንደሚኖር ገምተናል።ንፋስ ሲገባበት ክርፋቱ እየለቀቀ እንደሚሔድም እናምናለን ብለዋል።
የመጡት ሰዎችም ግርግሩ እንደሚቆም እንዲገነዘቡ መክረዋል።
ሰው ወደ ልቦናው ሲመልስ ዝላይና ጩኽቱ ይቆማል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የሃይልና የጉልበት አማራጭ እንደማይጠቅም መክረዋል።
ሶስት ጥይት ተኩሶ ግርግሩን መበተን ይቻላል ነገር ግን ይህ አያስፈልገንም መጠፋፋት ይበቃናል ብለዋል።
ጠቅላላ ተቃዋሚዎች ያላቸው ሃይል ከሃገሪቱ ጠቅላላ የጸጥታ ተቋምጋር ይቅርና ከአንድ ክልል ሃይል ያነሰ ነው ብለዋል።
ስለዚህ በጉልበት ማስፈጸም የሚቻል ነገር አይኖርም ሲሉ አሳስብዋል።
የአሸናፊና ተሸናፊ ፖለቲካ አብቅቶ ሁላችንም አሸናፊ የምንሆንበት የሰለጠነ ፖለቲካ ውስጥ እንግባ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።