(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 2/2011)የኢሕአዴግና አባል ድርጅቶቹ ጉባኤዎች ከአርብ ጀምሮ እንደሚካሄድ ታወቀ።
የኢሕአዴግ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በነገው ዕለት የሚካሄድ ሲሆን የኦሕዴድ 9ኛ መደበኛ ጉባኤ ደግሞ በሚቀጥለው ሳምንት በጅማ ከተማ እንደሚጀመር ተዘግቧል።
ብአዴን ሕወሃትና ደኢሕዴንም በተመሳሳይ ጉባኤያቸውን በዚሁ በመስከረም ወር እንደሚያደርጉም ተገልጿል።
በመጨረሻም የኢሕአዴግ ጉባኤ በሃዋሳ እንደሚካሄድም ተመልክቷል።
የፊታችን አርብ የሚጀመረው የኢሕአዴግ ምክር ቤት በኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ በቀረቡ አጀንዳዎች ላይ እንደሚወያይና በመስከረም ወር መጨረሻ ለሚካሄደው ጉባኤ አጀንዳ እንደሚቀርጽም ከድርጅቱ ድረ ገጽ ከተገኘው መረጃ መረዳት ተችሏል።
በተመሳሳይ ዜና የኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት ኦህዴድ ድርጅታዊ ጉባኤውን በሚቀጥለው ሳምንት በጅማ ከተማ ይጀምራል።ከ1ሺ በላይ ታዳሚዎች ይታደሙበታል የተባለው የኦሕዴድ ጉባኤ የድርጅቱን ስያሜና አርማ መለወጥን ጨምሮ የተለያዩ ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍም ተገልጿል።
ብአዴንም በጉባኤው በተመሳሳይ የስምና የአርማ ለውጥ ያደርጋል ተብሎ እየተጠበቀ ሲሆን በደኢሕዴን በኩል የታወቀ ነገር የለም።
ሕወሃት ግን ከነስምና አርማው እንደሚቀጥል ታውቋል።