(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 1/2011) በደቡብ ወሎ ዞን ወረኢሉ ወረዳ ህዝብ ያለመንግስት አስተዳደር ከአንድ ወር በላይ እንዳለፈው ተገለጸ።
ህዝቡ አስተዳዳሪዎቹን ከስልጣን ወርደው ለህግ ይቅረቡ የሚል ጥያቄ ማንሳቱን ተከትሎ በተፈጠረ ውዝግብ የወረኢሉ ወረዳ አመራሮች ሸሽተው ደሴ መግባታቸውንም የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
አመራሮቹ ህዝብን የበደሉ፣ የለውጡ እንቅፋት የሆኑ ናቸው በሚል የተነሳው ተቃውሞ መቀጠሉም ታውቋል።
አስተዳዳሪ የሌላት የወረኢሉ ወረዳ በህዝብ በተወጣጣ አመራር እየተመራች መሆኑን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
የአማራ ክልል መንግስት ችግሩን እያወቀ እስካሁን መፍትሄ አልሰጠም ሲሉ ነዋሪዎች ቅሬታ አቅርበዋል።
ከ100 ዓመታት በፊት የተቆረቆረችው ወረኢሉ ከደሴ በ85 ኪሎ ሜትር ትርቃለች። እንደሌሎቹ የአቅራቢያ አከባቢዎች ዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ስር የሰደዱባት ወረዳ ናት።
ባለፉት 27 ዓመታት ችግሮቹ ከመሻሻል ይልቅ ሌሎች ጭቆናዎች ተጨምረው ህበረተሰቡን ለከፍተኛ ምሬት እንደዳረጉት ነው ለኢሳት አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች የሚገልጹት።
ለዚህ ደግሞ በወረዳዋ አመራርነት የተቀመጡ ሰዎች የአንድ ቡድንን ጥቅም ከማስጠበቅ ያለፈ ለህበረተሰቡ የሰሩት ነገር የለም በሚል ከፈተኛ ተቃውሞ ሲቀርብባቸው ቆይቷል።
ባለፈው ሀምሌ ወር በእነዚህ አመራሮች አማካኝነት አንድ ውሳኔ መተላለፉን ደግሞ ታሞቆ የነበረውን የህዝብ ቁጣ እንዲፈነዳው አደረገው።
ወረኢሉ የወረዳ መዋቅር ተነጥቃ ለሌላ ሊሰጥ ውሳኔ ላይ የደረሱት አመራሮቹ ይህንን ለመግለጽ ህዝባዊ ስብሰባ ይጠራሉ። ከፍተኛ ተቃውሞም ይገጥማቸዋል።
ቀድሞውኑ አመራሮቹ ከስልጣን እንዲወርዱ የሚጠይቀው ህዝብ በውሳኔው በመቆጣት እርምጃ መውሰድ ጀመረ።
ተቃውሞ በወረዳዋ የተለያዩ መንደሮች ተስፋፋ። በአመራሮቹ ውሳኔ የተበሳጩ ወጣቶችም የአመራሮቹን መኖሪያ ቤቶች በማፍረስ ቁጣቸውን መግለጽ ቀጠሉ።
ሁኔታው ያስፈራቸው የወረኢሉ ወረዳ አመራሮችም ወደ ደሴ ከተማ መሸሻቸውን ነው የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው።
ካለፈው ሀምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ ወረኢሉ መንግታዊ መዋቅር እንደሌላት የሚገልጹት የኢሳት ምንጮች፡ ከህበረተሰቡ በተወጣጡ ሰዎች እየተመራች መሆኗን ጠቅሰዋል።
የደቡብ ወሎ አስተዳደር ጉዳዩን ለመፍታት ጣልቃ ቢገባም የአመራሮቹን መኖሪያ ቤቶች ያፈረሱ ወጣቶችን ለመያዝ በልዩ ሃይል አማካኝነት ሙከራ መደረጉ ውጥረቱን እንዳባባሰው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ህብረተሰቡ ወጣቶቹን አሳልፈን አንሰጥም፡ የህግ ጉዳይ ከሆነም እኛው ዘንድ መዳኘት ይችላሉ በማለት አቋም መያዙ ታውቋል።
ከአንድ ወር በላይ ከመንግስት መዋቅር የወጣችው ወረኢሉ ችግሩ እንዲፈታ ከበላይ አካል የደረገው ጥረት የለም ሲሉ ነዋሪዎቹ ይገልጻሉ።
የአማራ ክልል መንግስት ስለችግሩ በተደጋጋሚ እንዲያውቅ መደረጉን የገልጹት ነዋሪዎች ከአንድ ወር በላይ መፍትሄ ሳይሰጥ በመቆየቱ ለከፍተኛ ችግር መዳረጋቸውን ጠቅሰዋል።
ሁኔታውን በተመለከተ የደቡብ ጎንደር ዞን አስተዳደርን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።