(ኢሳት ዲሲ–ጳጉሜ 1/2010) የትግራይን ሕዝብ አንድነት ለማዳከም ሆነ ተብሎ የሚካሄድ በማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ተቀባይነት የለውም ሲል የክልሉ መንግስት ገለጸ።
የማንነት ጥያቄ ህገ መንግስታዊ መልስ ባገኘበት ሁኔታ አንድ ጊዜ ወልቃይት ሌላ ግዜ ራያ እያሉ የትግራይን ህዝብ አንድነት ለማዳከም አልሞ መስራት በማንኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የለውም ብሏል።
የራያ ተወላጆች ማንነታችን ይከበር በሚል በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄዳቸው ይታወሳል።
የትግራይ ክልላዊ መንግስት መግለጫ እንዳለው በአዲስ አበባ የተካሄደው የራያ ተወላጆች የማንነት ጥያቄና ሰላማዊ ሰልፍ ፀረ ህዝብ ነው፡፡
እንደ መግለጫው የራያ ህዝብን ክብር በሚነካ መልኩ የማንነት ጥያቄ አለን በሚል ፖለቲካዊ ዓላማ ባላቸው ሰዎች የሚመራ ቡድን በአዲስ አበባ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል።
ይህም የትግራይን ህዝብ ለማዳከም ከሚጠነሰሱ ሴራዎች አንዱና ሕገ-መንግስታዊ ጥሰትም ጭምር ነው ብሏል መግለጫው፡፡
የማንነት ጥያቄ ሲኖር ጥያቄ አለኝ የሚል ህዝብ ራሱ ያነሳል እንጂ እኔ አውቅልሃለሁ ማለት ጊዜው ያለፈበት ትእቢት ነው ያለው መግለጫው የፖለቲካ ዓላማ ያላቸው አካላት በከተማዎች መሽገው የሚያነሱት ጥያቄ የትም አይደርስም ሲልም አውግዟል።
ስለሆነም የማይመለከታቸው አካላት ስለ ማንነት ጥያቄ ማንሳታቸው ሞራላዊ ይሁን ህጋዊ መሰረት የለውም ነው ያለው መግለጫው፡፡
በመሆኑም የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ድርጊቱን በፅናት እናወግዛለን ብሏል።
በዚህ ተግባር እየተሳተፉ ያሉ አካላትንም በፅናት እንታገላቸዋለን ሲል የትግራይ ክልላዊ መንግስት መግለጫውን አጠቃሏል፡፡ የራያ ተወላጆች ማንነታችን ይከበር በሚል በአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄዳቸው ይታወሳል።
በዚሁም የትግራይ ክልል ልዩ ፖሊስ ሚሊሻዎችና የቀበሌ ታጣቂዎች የማንነት ጥያቄ ባነሱ የራያ ተወላጆች ላይ የሚፈጽሙትን የሰብአዊ መብት ረገጣ እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።
መከላከያና የፌዴራል መንግስት ጣልቃ እንዲገቡም መጠየቃቸው ነው የተነገረው።ጥያቄቸው መልስ እንዲያገኝም ለፌዴረሽን ምክር ቤት አቅርበዋል።