በቤንሻንጉል በተፈጠረ ግጭት የበርካታ ሰዎች ህይወት አለፈ

(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 28/2010) በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተፈጠረ ግጭት የበርካታ ሰዎች ህይወት አለፈ።

አሶሳ

በግጭቱ ከ 10 በላይ የቤንሻንጉል ሰዎችና የኦሮሞ ተወላጆች መሞታቸው ታውቋል።

ግጭቱ የተፈጠረው በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ዞን ኦዳ ቤልዲግ ወረዳ ደላቲ ከተማ መሆኑም ታውቋል።

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተፈጠረው ግጭት በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ህይወት ማለፉ ተነግሯል።

ከዚህ በተጨማሪም ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች ከቀላል እስከ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በመንዲ ሆስፒታል ህክምና እየተከታተሉ ይገኛሉ ተብሏል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ባወጣው መግለጫም ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ጋር በመሆን የግጭቱን መንስኤ በማጣራት አጥፊዎችን ለህግ ለማቅረብ  እየሰራ ነው።

በአሁኑ ወቅትም የፀጥታ አካላት እና ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመሆን ሁኔታውን ለማረጋጋት እየሰሩ መሆናቸውም ታውቋል።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት  በክልሉም ይሁን በሌላ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች እንዲረጋጉ አሳስቧል።

የቤንሻንጉል የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች ለኢሳት እንደገለጹት  የኦሮሞ ነጻነት ግንባር/ኦነግ/ ታጣቂዎች በአሶሳ ዞን ኦዳ ቤልዲግ ወረዳ ደላቲ ከተማ ገብተው በርካታ ነዋሪዎችን ገድለዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ግን በጉዳዩ ላይ እስካሁን የሰጠው መግለጫ የለም።