የሃረሪ ክልል ፕሬዚዳንት ከፓርቲው ስልጣን የለቀቁት በገዛ ፈቃዳቸው እንጅ ተገደው አለመሆኑን ገለጹ

የሃረሪ ክልል ፕሬዚዳንት ከፓርቲው ስልጣን የለቀቁት በገዛ ፈቃዳቸው እንጅ ተገደው አለመሆኑን ገለጹ
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 25 ቀን 2010 ዓ/ም ) ለኢሳት የደረሰው መረጃ እንደሚያሳየው የክልሉ ምክር ቤት ነሃሴ 23 ቀን 2010ዓም በተጠራበት ወቅት በኦህዴድና ሃብሊ ድርጅት መሪዎች አለመግባባት መፈጠሩን ያመለክታል። የሁለቱ ድርጅቶች አመራሮች መግባባት አለመቻላቸው በሚነገርም፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት ግን ይህንን ያስተባብላሉ።
ፕሬዚዳንቱ አቶ ሙራድ አብዱላሂድ ለኢሳት እንደገለጹት ሁለቱ ድርጅቶች ስምምነት መፈራረማቸውንና በጋራ መስራት መጀመራቸውን ተናግረዋል። አቶ ሙራድ የድርጅቱን መሪነቱን ስልጣን ማስረከባቸውንና ምክር ቤቱ ሲሰበሰብ የክልል መሪነት ስልጣናቸውን እንደሚያስረክቡ ተናግረዋል። አቶ ሙራድ ሁለተኛ የስልጣን ጊዜያቸውን እንደጨረሱ ስልጣን ለማስረከብ በተደጋጋሚ ጠይቀው እንደነበርና አሁን ተቀባይነት እንዳገኘ ተናግረዋል። ዶ/ር አብይ የጀመሩትን የለውጥ እርምጃ እንደሚደግፉት ገልጸዋል።