የአባይ ግድብ ሰራተኞች አድማ አደረጉ

(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 23/2010) የአባይ ግድብ ሰራተኞች የስራ ማቆም አድማ አደረጉ።

በገንዘብ እጥረት ምክንያት ስራው እየቀዘቀዘ የመጣው የአባይ ግድብ ፕሮጀክት በሰራተኞች በተነሳ የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄና በሚደረስባቸው የመብት ረገጣ ምክንያት አድማ እንደተመታበት የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

ከኢንጅነር ስመኘው በቀለ ግድያ በኋላ የአባይን ግድብ በሃላፊነት የተረከቡት አዲሱ ስራ አስኪያጅም የሰራተኛውን ጥያቄ መፍታት እንዳልቻሉ ምንጮች ጠቅሰዋል።

በትግራይ መልሶ ማቋቋሚያ ድርጅት ኢፈርትና በህወሃት ጄነራሎች በሚመራው ሜቴክ ከፍተኛ ዝርፊያ ተፈጽሞበታል የተባለው የአባይ ግድብ ፕሮጀክት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞቹን በቅርቡ ማሰናበቱም ታውቋል።

በአምስት ዓመት ያልቃል የተባለው የአባይ ግድብ ፕሮጀክት ስምንተኛ ዓመቱን አጠናቀቀ።

ያለፈው የህወሀት አገዛዝ በአረብ ሀገራት የተነሳው የለውጥ አብዮት ወደ ኢትዮጵያ ይገባል በሚል ስጋት ድንገት የተከሰተው የአባይ ግድብ ፕሮጀክት ያለበቂ የገንዘብ ዝግጅት፡ ግልጸነት በጎደለው አሰራር በመጀመሩ አሁን ለሚታየው መቋረጥና መዝረክረክ አስተዋጽኦ እንዳለው የቅርብ ምንጮች ይገልጻሉ።

በተለይም እንደዚህ ያለ ግዙፍ ፕሮጀክት ያለጨረታ ለአንድ ድርጅት መሰጠቱ፡ ከዚያም ጋር ተያይዞ የትግራይ መልሶ ማቋቋሚያ ድርጅት የሆነውን ኢፈርትንና በህወሀት ጄነራሎች ሲመራ የነበረውን ሜቴክ የተሰኘውን ተቋም በፕሮጀክቱ እቃ አቅራቢነትና የግንባታ ተቋራጭነት እንዲያዝ በማድረግ መጠነ ሰፊ የዝርፊያ ተግባር እንዲፈጸም መደረጉን መረጃዎች ያመልክታሉ።

ላለፉት ስምንት ዓመታት ከአባይ ግድብ ጋር በተለያዩ ሙያዎች ሲሰሩ የቆዩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰራተኞች በየጊዜው የሚደርስባቸውን አስተዳደራዊ በደልና የደምወዝ ማነስ ጥያቄ በተመለከተ ቅሬታ ቢያቀርቡም የሚሰማቸው ሳያገኙ ቆየተዋል።

በተለይም በተቋራጭ ድርጅቱ ሳሊኒ ኮንስትራክሽንና በሜቴክ አመራሮች የሚፈጸምባቸው በደልና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመደራረቡ ህልውናቸው አደጋ ላይ መውደቁን ነው ሰራተኞቹ የሚናገሩት።

በግድቡ ፕሮጀክት የጉልበት ሰራተኞች የምግብ አቅርቦት እንዲሁም ከሚሰሩት ስራ ጋር የማይመጣጠን የደምወዝ ክፍያ ምክንያት በየጊዜው ጥያቄ ሲያነሱ በሚስጢር በተዘጋጀ እስር ቤት እንዲገብ ተደርገው ስቃይ እንደሚፈጸምባቸውም ገልጸዋል።

በርካታ ሰራተኞች ጥያቄ ለምን አነሳችሁ ተብለው ከስራቸው እንደሚባረሩም ተመልክቷል።

ባለፈው ቅዳሜ ግን ሰራተኞች እርምጃ ወስደዋል። ለዓመታት የተጠራቀመውን ብሶት አድማ በመምታት እየገለጹ ነው።

ዛሬ ለአምስተኛ ቀን በቀጠለው የስራ ማቆም አድማ የግድቡ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ መቆሙን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

በግንባታው ተቋራጭ በኩል ከደመወዝ ክፍያ ማነስ በተጨማሪ የሰራተኛ አያያዝ፣ የምግብ ቤት የጥራት ችግርና የዋጋ መናርና ሌሎች ምክንያቶች ተጠቅሰው አድማው እንዲመታ እንዳደረገው ነው ለማወቅ የተቻለው።

የግድቡ ሰራተኞች በሙሉ ተሳትፈውበታል በተባለው በዚሁ አድማ በአስቸኳይ ምላሽ የሚሹ ጥያቄዎች ተነስተው ለሚመለከተው አካል እንዲቀርብ መታቀዱም ተገልጿል።

የአባይን ግድብ ከመጀመሪያው አንስቶ በስራአስኪያጅነት የመሩትና ባለፈው ወር የተገደሉት ኢንጅነር ስመኘው በቀለን ተክተው እየሰሩ ያሉት አቶ ኤፍሬም ወልደኪዳን ሰራተኞቹን አነጋግረው እንደነበረ የሚገልጹት የኢሳት ምንጮች በቃል ደረጃ ምላሽ ከመስጠት ያለፈ በተግባር የሚታይ ለውጥ ማምጣት እንዳልቻሉ ጠቅሰዋል።

አዲሱ ስራ አስኪያጅ በሰራተኛው የተጠየቁትን መሰረታዊ ጥያቄዎች መልስ መስጠት አለመቻላቸውን ተከትሎ የስራ ማቆም አድማው መመታቱን ምንጮች ካደረሱን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።