በቴፒ ከተማ 5 ሰዎች ተገደሉ

(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 23/2010 በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ 5 ሰዎች በደቡብ ክልል ልዩ ሃይል መገደላቸውን የኢሳት ምንጮች ገለጸ።

በአካባቢው ብሔርን ተኮር ያደረገ ግጭት ተባብሶ መቀጠሉን የአካባቢው ምንጮች አረጋግጠዋል።

ግጭቱን ለማብረድ የፌደራልና የክልል ባለስልጣናት ከዚህ ቀደሞ ወደ አካባቢው አምርተው ከሕዝቡ ጋር ቢመክሩም ችግሩ አሁንም መፍትሄ አላገኘም ተብሏል

በሸካ ዞን ቴፒ ከተማ ልዩ ልዩ ብሔረሰቦች በመተሳሰብና በአንድነት ለበርካታ ዘመናት አብረው ኖረዋል።

ባለፉት 27 አመታት በነበረው የብሔር ፖለቲካ ግን በአካባቢው የሚኖሩ ብሔረሰቦች በጥርጣሬ እንዲተያዩ ተደርገዋል።

በሸኪቾ ብሔረሰብ አስተዳደር አባላት በራአገዛዝ አስተዳደር ስም ሌሎችን ሲጨቁኑና ሲበድሉ መኖራቸውን የአካባቢው ምንጮች ይናገራሉ።

በዚህም ምክንያት እስር ይብቃን በሚል የተለያዩ ብሔረሰቦች በየች ወረዳና በቴፒ አስተዳደር አካላት የሚደርስባቸውን በደል በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል።

የሸኪቾ ብሔረሰብ አባላት በበኩላቸው ሌሎችን በመቃወም ከአካባቢው ውጡልን በሚል ግጭት ሲፈጥሩ መቆየታቸው ነው የሚነገረው።

የኢሳት ምንጮች እንደሚሉት ባለፈው ሳምንት ሰኞችና ማክሰኞ በተካሄደ የተቃውሞ ሰልፍ ግጭት ተቀስቅሶ እስካሁን አልበረደም።

እናም በዚሁ ግጭት ሳቢያ በጠቅላላው 5 ሰዎች ተገድለዋል ብለዋል።

መከላከያና ፌደራል ፖሊስ ሰላም ለማስከበር ጥረት ቢያደርጉም አካባቢው አሁንም ከግጭት ነጻ የሆነ ቀጠና አለመሆኑን የኢሳት ምንጮች ይናገራሉ።

ጥቃቱን የሚያደርሱት የደቡብ ክልል ልዩ ሃይል አባላት ናቸው ይላሉ

የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ወረዳው በሸካዎች ስለሚተዳደር የሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች  መብት እየተከበረ አይደለም።

በሸክቾ ዞን ቴፒ ከተማ የተቀሰቀሰውን ግጭት ለማብረድ የፌደራልና የክልል ባለስልጣናት ወደ አካባቢው ቢያመሩም እስካሁን ሰላም አልተገኘም ተብሏል።

እናም በሸክቾ ዞን ቴፒ የተከሰተውን ግጭት ለማርገብ መንግስት ጣልቃ እንዲገባ የልዩ ልዩ ብሔረሰብ አባላት ጠይቀዋል።

የሸካ ብሔረሰብ አባላት በበኩላቸው ከኖርንበር አካባቢ ተነቅለን እንድንወጣ በሌሎች ብሔረሰብ አባላት ግፊት እየተደረገብን ነው የሚል ቅሬታ ያቀርባሉ።