(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 22/2010) በሶማሌ ክልል ምክር ቤት ያለመከሰሰ መብታቸው የተነሳባቸው 6 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተሰማ።
በቁጥጥር ስር የዋሉት 6ቱ ሰዎች በአብዲ ኢሌ አስተዳደር ውስጥ ቁልፍ የሚባሉ ቦታዎችን ይዘው የነበሩ መሆናቸውም ታውቋል።
ምክር ቤቱ የቀድሞ የክልሉ ፕሬዝዳንት አብዲ ኢሌን ጨምሮ የክልሉን 7 ከፍተኛ አመራሮች ያለመከሰስ መብት ያነሳው ባለፈው እሁድ ነበር።
በሶማሌ ክልል ያለው ኢሰብአዊ ድርጊት ይቁም፣የዜጎች አላግባብ መጨቆን ሊያበቃ ይገባል፣በክልሉ ያለው ልዩ ሃይል በዜጎች ላይ የሚያደርሰው የመብት ጥሰት ሊቆምና ልዩ ሃይሉም ሊወገድ ይገባዋል የሚሉት የአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት ተደጋጋሚ ጥያቄ ነበር።
ተቋማቱ ያንን ጥያቄ በተደጋጋሚ ቢያነሱም የአብዲ ኢሌ የግፍ አገዛዝ ግን ማክተሚያ የሚያገኝ አይመስልም ነበር።
ባለፈው እሁድ የክልሉ ምክር ቤት ያሳለፈው ውሳኔ ግን የአብዲ ኢሌ አስተዳደር ወደ ተጠያቂነት የሚያሸጋግር ነው ሲሉ በርካቶች አስተያየታቸውን ሰጡ።
ምክር ቤቱ የቀድሞ የክልሉ ፕሬዝዳንት አብዲ ኢሌን ጨምሮ ቁልፍ የሚባሉትን የአብዲ ኢሌን 6 ከፍተኛ አመራሮች ያለመከሰስ መብት አንስቼያለሁ የሚል ነው።
ከስፍራው ኢሳት ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ሌሎች በአብዲ ኢሌ የአስተዳደር ዘመን በወንጀል ተሳትፈዋል የሚባሉ ግለሰቦችን የማጥራቱ ስራ ተጠናክሯል።
በአብዲ ኢሌ ቤተሰቦችና ጎሳዎች ተሞልቷል የሚባለው የቀድሞ አስተዳደር ከሰብአዊ መብት ጥሰት ጀምሮ በሌብነትና በሌሎች ተያያዝ ጉዳዮች ተባባሪ እንደነበር የሚያሳዩ መረጃዎች ሲወጡ ቆይተዋል።
አሁን ላይ ሌሎች የወንጀሉ ተባባሪዎችን የማጥራቱ ስራ በነዚህ መረጃዎች ላይ የተመሰረተ መሆኑም ተመልክቷል።
እንደ መረጃው ከሆነም አብዲ ኢሌን ጨምሮ በቁጥጥር ስር የዋሉት የ6ቱ ከፍተኛ አመራሮች ጉዳይ በቅርቡ ፍርድ ቤት ቀርቦ እንደሚታይም ታውቋል።
ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ሶማሌ ላንድ ተሸሽገው የነበሩ ሁለት የአብዲ ኢሌ ካቢኒ አባላት ወደ ሞቃዲሾ ለመሄድ ሲሞክሩ በአውሮፕላን ማረፊያ ተይዘዋል።
በቅርቡ በጅጅጋና በአካባቢው በአብዲ ኢሌ የወንጀል ተባባሪዎች የተፈጸመው ኢሰብአዊ ድርጊት ምን ያህል ጥልቀት እንደነበረው በአካባቢው ከነበረው የኢንተርኔት አገልግልግሎት መቋረጥ ጋር ተያይዞ ማወቅ አልተቻለም ነበር ይላሉ የኢሳት ምንጮች።
አገልግሎቱ መጀመሩን ተከትሎ እየወጡ ያሉትና የአብዲ ኢሌን የለየለት ኢሰብአዊ ድርጊት የሚያሳዩት ምስሎች አብዲ ኢሌን በጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለማቅረብ ማስረጃ ናቸው ይላሉ ምንጮቹ።