የቀድሞው የሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት በቁጥጥር ስር ውለው ወደ እስር ቤት ተወሰዱ
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 21 ቀን 2010 ዓ/ም ) ባለፉት 10 አመታት በሶማሊ ክልል ለደሰው የሰው እልቂት፣ የሰብአዊ መብት ጥሰትና ስደት በዋነኝነት ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚነገርላቸው የቀድሞው የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ ሙሃመድ ኡመር በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው ወደ እስር ቤት ተወስደዋል። አቶ አብዲ በተለያዩ ከባድ ወንጀሎች እንደሚጠየቁ ታውቋል። የተለያዩ አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ሳይቀሩ አቶ አብዲ በቁጥጥር ስር ውለው ለፍርድ እንዲቀርቡ ሲጠይቁ ቆይተዋል። በመጨረሻ ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ውለው መታሰራቸው የዶ/ር አብይ አህመድ መንግስት በወንጀል የሚጠየቁ ሰዎችን በመደመር ስም ምህረት እየሰጠ ከወንጀላቸው እንደማያነጻቸው ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።
በሌላ በኩል ደግሞ ብአዴን ክልሎች የህዝብ ፍላጎት ባማከለ መልኩ እንደገና እንዲዋቀሩ ጠይቋል። የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጥያቄም ከብአዴን ፍላጎት ውጭ ሲከናወን በመቆየቱ እንደገና እንዲታይ ወስኗል።
በአቶ ገዱ አንዳርጋቸውና በአቶ ደመቀ መኮንን የሚመራው ብአዴን ከጥቂት ቀናት በፊት በሁለት ከፍተኛ አመራሩ ላይ የእግድ እርምጃ ወሰደ። በአቶ በረከት ስምዖን እና በቅጽል ስማሸው “ጥንቅሹ” ተብለው በሚጠሩት በአቶ ታደሰ ካሳ ላይ።
ድርጅቱን ከሁለት አስርት አመታት በላይ ሲዘውሩት የቆዩት ቱባ ሹመኞች እርምጃው የተወሰደባቸው፣ እንደ ድርጅቱ መግለጫ፡- ለሕዝብን ጥቅም አለመቆማቸው በመረጋገጡ እና ከጥረት ኮርፖሬሽን ጋር በተያያዘ ነው።
ስለተወሰደባቸው እርምጃ በአሶሺየትድ ፕሬስ የተጠየቁት አቶ በረከት ስምዖን “እርምጃው መሰረተ ቢስ ነው” በማለት እንደማይቀበሉት ቢገልጹም፤ ብአዴን ግን የለውጡ እንቅፋት በሆኑ ላይ ሁሉ የማስተካከያ እርምጃዎችን በመውሰድ ወደፊት እንንደሚቀጥል ነው ያስታወቀው።
ይህ ብቻ ሳይሆን በጥቂት ከፍተኛ አመራሮች ሲዘወር በቆየው እና ለጥቂቶች ብልጽግና የሙስና በር እንደከፈተ ሲወራበት በነበረው ጥረት ኮርፖሬሽን ላይ ድርጅቱ የፖለቲካ ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቋል። “የጥረት ኮርፖሬሽን ሀብት የሕዝብ ሀብት በመኾኑ ከእንግዲህ የኮርፖሬሽኑ ተጠሪነት ለክልሉ መንግስት ይሆናል” የሚል ፖለቲካው ውሳኔ።
ብአዴን ከዚህም ባሻገር በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ባለው የድንበር ማካለል ዙሪያም ጠንካራ ውሳኔ አሳልፏል።
“ የድንበር ማካለሉ በዘላቂነት እስኪፈታ ድረስ የሁለቱም ወገን አርሶ አደሮች የያዙትን የእርሻና የደን መሬት እንደያዙ እየተጠቀሙ እንዲቆዩ በመንግስታቱ መካከል ስምምነት ቢፈረምም ፤ በተለይ በመተማ ወረዳ ልዩ ስሙ ደለሎ በተባለው አካባቢ ታሪካዊ ዳራውንና ነባር የይዞታ መብታችንን ያላስጠበቀ፣ የሚመለከታቸውን አካላት ያላሳተፈና የጋራ አቋምም ያልተያዘበት ውሳኔ ተሰጥቶ እንደነበር አውቀናል” ያለው ብ አዴን፣ “ይህ ውሳኔ ብአዴንና አመራሮቹ ለረጅም ጊዜ በህዝብ ዘንድ ባልተገባ መልኩ ሲታሙና ሲጠረጠሩ እንዲቆዩ አድርጓል፡፡ በመሆኑም ውሳኔው በፌዴራል መንግስት በኩል አስቸኳይ ማስተካከያ እንዲደረግበት እንጠይቃለን”ሲል አሣስቧል።
ቀደም ባሉት ዓመታት ለሱዳን ተቆርሶ ተሰጥቷል በተባለው መሬት ዙሪያ ፊርማቸውን አኑረዋል በሚል የብ አዴኑ አቶ ደመቀ መኮንን እና ሌሎች አመራሮች ከፍተኛ ወቀሳ ሲደርስባቸው መቆየቱ ይታወሳል። ይሁንና በቅርብ የወጣው ተጨባጭ መረጃ በስምምነቱ ላይ ፊርማውን ያኖሩት የህወኃቱ አቶ አባይ ጸሀዬ መሆናቸው ተመልክቷል።
እንደ ድርጅቱ መግለጫ፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ለጋራ የጸጥታ ማሰከበር ስራ ይጠቅማል የሚለውን ስምምነት ምክንያት በማድረግ በቋራ ወረዳ ልዩ ስሙ ነፍስ ገበያ በተባለው አካባቢ ለጊዜው ሰፍሮ የነበረው የሱዳን ወታደር፣ ይዞታ እያሰፋፋና ቋሚ ካምፕ እየገነባ ከያዘው ጊዚያዊ ይዞታ ሳይለቅ መቆየቱ ተገቢ እንዳልሆነ ማዕከላዊ ኮሚቴው ገምግሟል።
“ የካምፑ መኖር የድንበሩን ጉዳይ የበለጠ እያወሳሰበውና የክልሉ አርሶ አደሮችም የእርሻ ስራቸውን በሰላም እንዳያከናውኑ እንቅፋት እየሆነ ይገኛ” ያለው የብአዴን መግለጫ፤ ከዚህ አኳያ የሱዳን ወታደር እስካሁን ድረስ ከያዘው ይዞታ ለቆ አለመውጣቱ ተገቢ ባለመሆኑ በፍጥነት ከይዞታችን ለቆ እንዲወጣና የፌዴራል መንግሥትም ይህንኑ እንዲያሰፈጽምልን እንጠይቃለን” ብሏል።
በድርጅቱ የተደረገውን መተካካት ባለመደገፋቸው እና በአቋማቸው የማይደራደሩ በመሆናቸው ሳቢያ እርምጃ እንደተወሰደባቸው የተናገሩት አቶ በረከት፣ ላለፉት 27 ዓመታት ሲዘውሩት ከቆጡበት ድርጅት በዘራቸው ምክንያት እንደተባረሩ መናገራቸው ብዙዎችን አስገርሟል። ምክንይቱም አቶ በረክት በዘራቸው ኤርትራዊ መኾናቸው የሚታወቀው ዛሬ አይደለም። ቃለ ምልልሱን የተመለከቱ አንዳንድ አክቲቪስቶች ፣ለዓመታት ድርጅቱን ሢመሩ የቆዩት አቶ በረከት ዛሬ ይህን ካርድ መምዘዛቸው፤ በቅርቡ ዶክተር አብይ ግለሰቦች ወንጀል ፈጽመው ሲጠየቁ ብሔራቸው ውስጥ እንዳይደበቁ ልንነቃባቸው ይገባል ያሉትን የሚያስታውሰን ነው ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ትናንት ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ከአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጋር ስብሰባ የተቀመጡት የአማራ ክልል ምሁራን ‹‹ዘረኝነት በኢትዮጵያዊ እሳቤ መጥፋት አለበት››ማለታቸውን የአብመድ ወኪል ታርቆ ክንዴ ዘግቧል።
ምሁራኑ በባሕር ዳር እየተካሄደ ባለው ውይይት ላይ ካነሷቸው ነጥቦች መካከል ፦‹‹ማንም ይምጣ ኢትዮጵያን በጋራ እንገነባለን፣አባቶቻችን ታሪካችን ጣፋጭ እንዲሆን አድርገዋል፤እኛም ይሄን ጣፋጭ ታሪክ ማስቀጠል አለብን፤የትም እንሂድ ኢትዮጵያን በጋራ እንገነባለን፣እውቀት እና ክህሎት ታላቅ ገዢ ነው፣ ዘረኝነት እውቀትን እየተጫነ ነው፡፡ ስለሆነም ዘረኝነት በኢትዮጵያዊ እሳቤ መጥፋት አለበት”የሚሉት ይገኙበታል።
በሌላ በኩል ድርጅቱን የማጥራት እርምጃ እየወሰደ ያለው እና አክቲቪስት ሙስጠፋ ኡመርን ክልሉን እንዲያስተዳድር የሾመው የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ከሰባት የምክር ቤቱ ባለሥልጣናት ላይ ያለመከሠስ መብታቸውን አንስቷል።
በክልሉ በተፈጸሙ የሰብ ዓዊ መብት ጥሰት እና የተለያዩ ከባድ ወንጀሎች እጃቸው እንዳለበት ከሚጠረጠሩትና ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ ከተደረጉት መካከል የቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር አብዲ ኢሌይ አንዱ ናቸው።
ይህን ተከትሎ አብዲ ኢሌይ ዛሬ አትላስ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው አሁን በፌዴራል ፖሊስ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
ዓለማቀፉ የሰብ ዓዊ መብት ተሟጋች ሁዩማን ራይስት ዎች የዶክተር አብይ አስተዳደር አቶ አብዲ ኢሌይን ለህግ እንዲያቀርባቸው በተደጋጋሚ መሣሰቡ ይታወቃል።
ከጥቂት ቀናት በፊት የክልሉ የፍትህ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ የነበሩ ሁለት ባለሥልጣናት አብዲ ኢሌይ ከስልጣን መወገዳቸውን ተከትሎ ያለ ህጋዊ መጓጓዣ ሰነድ ወደ ሀርጌሳ ሲያመልጡ በሶማሌ ላንድ የአሚግሬሽንና ደህንነት ባለሥልጣናት ተይዘው መታሰራቸው ተዘግቧል።