የጳጉሜ ወር የአገራዊ እርቅ ወር ለማድረግ ጥሪ ቀረበ
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 18 ቀን 2010 ዓ/ም ) የአገራቸው ጉዳይ ያሳሰባቸው ኢትዮጵያውያን ፣ አገራችን የጀመረቸው በጎ ጎዳና ቀጣይነት ባለው መልኩ ውጤታማ ሆኖ ሁላችን ልናያት የምንመኛት ኢትዮጵያን ለመፍጠር ህዝባችን ወደ ተሻለና ዘለቄታዊነት ወዳለው ህብረትና አንድነት እንዲመጣ የጻጉሜ ወር የእርቅ ረው እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያውያኑ ለጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ በላኩት ደብዳቤ፣ አብያተ እምነቶች እርቅን እንዲያውጁ፣ እርቅን እንዲያስተምሩና ስለ እርቅ እንዲጸልዩ፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ስለ እርቅ እንዲዘምሩ፣ የመገናና ብዙሃን ያለመታከት በዚህ ዙሪያ መልዕክቶችን እንዲያስተላልፉ በማድረግ ፣ በውስጣችን ተደብቆ ከተቀመጠው ቂምና የበቀል ሃሳቦች ሁሉ ተላቅቀን በፍቅርና በጠነከረ ኢትዮጵያዊ ወንድማማችነትና አንድነት መጪውን 2011 ዓም የሚጀመርበት ሁኔታ ለመፍጠር ማሰባቸውን ገልጸዋል።
በጳጉሜ ሳምንት የኢትዮጵያ ህዝብ ስለ እርቅ እንደሚነጋገር፣ እንደሚመክርና እንደሚዘከር በመግለጫው የተጠቀሰ ሲሆን፣ መርሃ ግብሩ የቀደሙት በደሎችና ጥፋቶች እንደ መዋቀሻና መካሰሻ የማይነሱበትን እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ በህዝቡ ስም ተነሳን የሚሉ የፖለቲካ ሰዎች፣ ፓርቲዎችና ስርዓቶች መሰል ጥፋት በአገራችን በማይደገምበት ሂደት ዙሪያ የኢትዮጵያ ህዝብ ቃል ኪዳን ይገባል ተብሎአል።