(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 11/2010) የሶማሌ ክልል የሀገር ሽማግሌዎችና ህዝቡ በጅጅጋና በሌሎች የክልሉ ከተሞች የተቃጠሉትን አብያተክርስቲያናት መልሶ ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመራቸው ተገለጸ።
በደገሃቡር ከተማ ከትላንት በስቲያ በተካሄደ ህዝባዊ ስብሰባ በአብዲ ዒሌ ተከታዮች የተፈጸመውን ጥቃት ዳግም እንዳይከሰት ለማድረግ ቃል መገባቱንም የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።
በጥቃቱ የተጎዳውን ህዝብና የወደሙትን አብያተክርስቲያናት ለማቋቋም ሰፊ ስራ እንዲጀመር ከስምምነት ላይ መደረሱን ለማወቅ ተችሏል።
ዛሬም በጅጅጋ ተመሳሳይ ህዝባዊ ስብሰባ መደረጉን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ከአንድ ቀን በፊት የተካሄደውም ስብሰባ የሶማሌ ክልል የሃገር ሽማግሌዎችና ህዝቡ በጅጅጋና በሌሎች የክልሉ ከተሞች የተቃጠሉትን አብያተክርስቲያናት መልሰው እንደሚገነቡ ቃል ገብተዋል።–ለዚህም ግንባታቸው የሚሆን እንቅስቃሴ መጀመሩንም ነው ይፋ ያደረጉት።
ደገሃቡር ላይ ተካሄደ በተባለው በዚህ ህዝባዊ ስብሰባ በአብዲ ኢሌ ተከታዮች የተፈጸመው ጥቃት ዳግም እንዳይከሰት ተሰብሳቢዎቹ ቃል መግባታቸውም ታውቋል።
በሌላ በኩል በሶማሌና ኦሮሚያ ክልሎች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ግድያ ውስጥ ተሰማርቶ የነበረው የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል አዛዥ ከመንግስት ጋር አብረው እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
አዛዡ የአብዲ ዒሌን ከስልጣን መወገድ ተከትሎ ሽላቦ አከባቢ ተሸሽገው ልዩ ሃይሉን ሲመሩ ከቆዩ በኋላ በህዝብ ግፊት ከተደበቁበት ወጥተው መግለጫ መስጠታቸውን ነው የኢሳት ምንጮች የገለጹት።
አለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተቆርቋሪ ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዎች በቅርቡ ባወጣው ሰፊ ሪፖርት ላይ የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይልን ማፍረስ እንደሚገባ የምክር ሃሳብ ለመንግስት ማቅረቡ የሚታወስ ነው።
ከአብዲ ዒሌ ከስልጣን መወገድ በኋላም በጥፋት መንገዱ ቀጥሎ በኦሮሚያ ክልል የ42 ሰዎችን ህይወት ባጠፋው የሶማሌ ክልል ልዩ ሃይል ላይ የፌደራል መንግስቱ የሚወስደው ርምጃ ሊኖር እንደሚችል ከምንጮች መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
ርምጃው ምን እንደሆነ ግን ለጊዜው አልታወቀም።