(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 10/2010) በምስራቅ ጎጃም ዞን የሚገኙ ሁለት ትምህርት ቤቶች ስማቸው ሊቀየር መሆኑ ተገለጸ።
በአቶ መለስ ዜናዊና በግንቦት 20 ሲጠሩ የነበሩት ትምህርት ቤቶች ስያሜያቸው እንዲቀየር መወሰኑን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በሸበል በረንታና በአዋበል ወረዳዎች የሚገኙት የሁለተኛ ደረጃና የመሰናዶ ትምህርት ቤቶች እስካሁን ሲጠሩበት የነበሩበት ስያሜዎች የሚወክሉን አይደሉም በሚል እንዲቀየሩ ነው ከስምምነት የተደረሰው።
በሌላ በኩልም በባህርዳር የሚገኘውና በግንቦት 20 ስም የሚጠራው አውሮፕላን ማረፊያ ስሙ እንዲቀየር እንደሚፈልጉ ኢሳት ያነጋገራቸው የባህርዳር ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ምስራቅ ጎጃም ዞን ሸበል በረንታ ወረዳ የሚገኘው አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ላለፉት በርካታ ዓመታት ሲጠራ የነበረው ሸበል መለስ ራዕይ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በሚል ነበር።
የወረዳው ምክር ቤት በትላንትናው ዕለት ባደረገው መደበኛ ስብሰባ ላይ የስያሜ ለውጥ እንዲደረግ የቀረበውን ሀሳብ ተቀብሎታል።
በዚህም መሰረት መለስ ራዕይ የሚለው ወጥቶ ሸበል አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በሚል እንዲጠራ ተወስኗል።
ትምህርት ቤቱ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በስያሜው ላይ የህዝብ ቅሬታ እንደነበር ተገልጿል።
የስያሜ ለውጡ ያስፈለገበት ምክንያትም ትምህርት ቤት የህዝብ በመሆኑ ስያሜውም ማህበረሰቡን ያማከለ መሆን ስለሚገባው መሆኑን በምክርቤቱ ስብሰባ ላይ መነሳቱን ነው የደረሰን መረጃ ያመለከተው።
በዚያው በምስራቅ ጎጃም ዞን በአዋበል ወረዳ ሉማሜ ከተማ የሚገኘው ግንቦት 20 አጠቃላይና ከፍተኛ መሰናዶ ትምህርት ቤት በህበረተሰቡ ጥያቄ መሰረት ስያሜ እንዲቀየር መደረጉን ለማወቅ ተችሏል።
የሃይማኖት አባቶች፣ የእድር ተወካዮች፣ የከተማ ታዋቂ ግለሰቦች ከወረዳዋ አመራሮች ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ እንደተገለጸው ግንቦት 20 የሚለው ስያሜ የማህበረሰቡን ፍላጎት በመጫን በሌሎች አካላት የተሰየመ በመሆኑ በአስቸኳይ መቀየር እንዳለበት በሙሉ ድምጽ ከስምምነት ላይ ተደርሷል።
በመሆኑም ግንቦት 20 የሚለው ስም እንዲወጣና ከሚቀጥለው የኢትዮጵያ አዲስ አመት 2011 ጀምሮ የትምህርት ቤቱ ስያሜ ሉማሜ አጠቃላይና ከፍተኛ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተብሎ እንዲጠራ የአዋበል ወረዳ ምክር ቤት ውሳኔ ማስተላለፉ ታውቋል።
በሌላ በኩልም የባህርዳር ግንቦት 20 አውሮፕላን ማረፊያ መጠሪያው እንዲቀየር ግፊት እንዳለ ለኢሳት የደረሱ መረጃዎች አመልክተዋል።
አንዳንድ ኢሳት ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንደሚሉት ግንቦት 20 በሚል የሚጠራው የባህርዳር አውሮፕላን ማረፊያ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ ፈጥሯል።
በብአዴን አንዳንድ አመራሮች ዘንድም ጉዳዩ በቁጭት የሚነሳ መሆኑን የገለጹት የኢሳት ምንጮች ስያሜው እንዲቀየር የሚደረገው ግፊት መጨመሩን ለማወቅ ተችሏል።
በቅርቡ በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚገኘው የአቶ መለስ ዜናዊ ፎቶግራፍ በተቃውሞ እንዲወርድ መደረጉ የሚታወስ ሲሆን በተለያዩ የኦሮሚያ አከባቢዎች በአቶ መለስ ዜናዊ የተሰየሙ ፓርኮች ስያሜው የተሰቀለባቸው ታፔላዎች መፍረሳቸውም ሲዘግብ ቆይቷል።
በበርካታ አብያተ ክርስቲያናት የተሰቀሉት የአቶ መለስ ዜናዊ ፎቶግራፎችን በተመለከተም ተቃውሞዎች እየተሰሙ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።