(ኢሳት ዲሲ–ነሀሴ10 /2010) የአማራ ክልል ልዑክ በአስመራ ከተማ ከአማራ ዲሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ /አዲሃን/ ጋር ምክክር መጀመሩ ተነገረ፡፡
አዴኃንና የአማራ ክልል መንግስት ልኡካን የአማራን ህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡበት ጉዳይ ላይ እየመከሩ መሆኑም ታውቋል
በቅርቡ የአዴኃን አመራሮች በሰላም ለመታገል በመወሰናቸው ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው ከምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን እና ከአማራ ክልል ገዱ አንዳርጋቸው ጋር መምከራቸው ይታወሳል።
በዚሁም አዲሃን ወደ ሀገሩ ገብቶ በሰላም እንዲንቀሳቀስና ጥሩ አጋር ሆኖ እንዲሰራ የክልሉ መንግስት ድጋፍ እንደሚያደርግለትም ቃል ተገብቶለት ነበር፡፡
ወደ ኤርትራ አስመራ የተጓዘውን የልኡካን አባል ቡድን የመሩት የክልሉ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ ጥላሁን ከአዴኃን አመራሮች ጋር ሲመክሩ የኤርትራ መንግስት ጉዳዩ በሰላም እልባት እንዲያገኝ ያሳየውን አጋርነት አድንቀዋል፡፡
አዴኃንና የአማራ ክልል መንግስት ልኡካን የአማራን ህዝብ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡበት ጉዳይ ላይ መክረዋል ቢባልም ሁለቱ ወገኖች በዝርዝር ስለተነጋገሩበት ጉዳይ ግን በግልጽ የተቀመጠ ነገር የለም።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኡስማን ሳሌህ ‹‹መንግስት የሰላም ድርድሩን ይደግፋል፤በኤርትራ የሚገኙ ነፍጥ ያነሱ የፖለቲካ ድርጅቶችም ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በሰላም እንዲታገሉ ሀገራችን ትሰራለች›› ማለታቸው ተሰምቷል።
ኢዴኃን ራሱን ለድርድር ዝግጁ በማድረጉ እና የአማራ ክልል መንግስትም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠቱ ምስጋናቸውንም አቅርበዋል ፡፡
የኤርትራ መንግስት ድርጅቶቹ ወደ ሀገራቸው ገብተው እንዲንቀሳቀሱ በሚደረገው ጥረት ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡
የአማራ ዲሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ /አዲሃን/ ካለፉት 8 አመታት ወዲህ መሰረቱን በኤርትራ በማድረግ የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ መቆየቱ ይታወቃል።