በአዳማ ከተማ በተፈናቃዮችና በአካባቢው ማኅበረሰብ መካከል በተፈጠረ ግጭት የተወሰኑ መጠለያ ቤቶች ተቃጠሉ።
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 07 ቀን 2010 ዓ/ም ) ተፈናቃዮቹ ህገወጥነትን እያስፋፉ ነው ሲሉ ነዋሪዎች ይከሳሉ። ተፈናቃዮች በበኩላቸው መንግስት የገባልንን ቃል ያክብር፤ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንገኛለን ብለዋል።
ከሶማሌ ክልል በአብዲ ኢሌ ልዩ ተዕዛዝ ለዘመናት ከኖሩበት ቀያቸው በግዳጅ ተፈናቅለው በአዳማ ከተማ በመንግስት በተሰራላቸው መጠለያ ቤቶች ውስጥ ነዋሪ በሆኑት ተፈናቃዮችና በአካባቢው ነዋሪዎች መካከል ግጭት ተቀሰቀሰ። በግጭቱም የተፈናቃዮቹ የተወሰኑ መጠለያ ቤቶች በእሳት መቃጠላቸው ታውቋል። ለግጭቱ መቀስቀስ ተፈናቃዮቹ በተደጋጋሚ ጊዜያት የሚፈጽሙት ህገወጥ ዝርፊያና ሥርዓት አልበኝነት መሆኑን ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።
በአካባቢው ገንደ ጋራ ልዩ ስሙ ዶሮ እርባታ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው ነዋሪዎች እንዲሁም በግብርና ሙያ በሚተዳደሩት የቀጨማና አካባቢው አርሶ አደሮች እህል ወደ ገበያ ይዘው በሚመጡት ወቅት ይዘረፋሉ፤ አካላዊ ጥቃቶችም ይደርስባቸዋል። በከተማዋ መውጫ ላይ በድንጋይ መጥረብ ካባና አሸዋ ሥራ ላይ በህጋዊነት የተሰማሩት ሰራተኞችን ጨምሮ አሽከርካሪዎችን በግዳጅ ክፍያ እንዲፈጽሙ ይጠየቃሉ። ይህን ህገወጥነት በማይቀበሉት ላይም ጥቃት ለማድረስ ዛቻና ማስፈራሪያ እንደሚደርስባቸው ነዋሪዎቹ በምሬት መናገራቸውን ምንጮቻችን አስታውቀዋል። በተለይም ፍልሰተኞቹ ነዋሪዎች ላይ የሃይማኖታዊ ግጭት የማስነሳት ስጋት መፍጠራቸው ለትናትናው እረብሻ መቀስቀስ ምክንያት ሆኗል።
በከተማዋ ዳርቻ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተክርስቲያን የሆነውን ቅዱስ መርቆሪዮስ ቤተክርስቲያን ለማቃጠል ሙከራ ማድረጋቸው፤ የሃይማኖት አባቶች ላይ በተደጋጋሚ ጊዜያት ትንኮሳዎች መፈጸማቸው ምእመናኑንና ነዋሪዎችን አሳዝኗል። ቤተክርስቲያኗ ምእመናኑንና አርሶ አደሮችን በማስተባበር የምግብና የአልባሳት እገዛ በማድረግ ስትታደጋቸው ቆይታለች። ‘’ለዚህ መልካም ውለታችን ይሄን ዓይነት ወንጀል ሊታሰብብን አይገባም ‘’ ብለዋል።
አክለውም ‘’በተደጋጋሚ ለፖሊስና የጸጥታ አካላት ብናመለክትም ወንጀለኞቹ ተይዘው ካለምንም ህጋዊ ቅጣት በነጻ ይለቀቃሉ። ፍትህ ልናገኝ አልቻልንም። ይህን ተከትሎ እራሳችንን ከጥቃት ለመከላከል ተገደናል። መንግስት አፋጣኝ መፍትሔ ይስጠን።’’ ሲሉ የከተማው ነዋሪዎች እና አርሶ አደሮች ብሶታቸውን አሰምተዋል። በዚህም ምክንያት በተፈጠረ ግጭት የእሳት ቃጠሎ ተነስቶ የተፈናቃዮች የተወሰኑ መኖሪያ ቤቶች በእሳት መቃጠላቸውንና አሁንም በጸጥታ ሃይሎችና በተፈናቃዮች መሃከል ውጥረት መንገሱን ምንጮቻችን ገልጸዋል።
ተፈናቃዮቹ በበኩላቸው ከቀጨማ ተራራ ሥር ጣራና ግድግዳው ቆርቆሮ በቆርቆሮ በተሰራ መኖሪያ ቤት ውስጥ በጋውን በሃሩር፤ ክረምቱን በቁር እንዲሰቃዩ መደረጋቸውን ይናገራሉ። መንግስት ከዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ግብረሰናይ ድርጅቶችና በስማቸው የሰበሰውን ገንዘብና እርዳታ እንዳልሰጣቸውና ሕይወት ከባድ እየሆነባቸው መምታቱን በተለይም ታዳጊ ሕጻናት፣ በዕድሜ የገፉ አቅመ ደካማ አዛውንቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ የአልጋ ቁራኛ የሆኑ ህመምተኞች ለርሃብና እርዛት ተጋላጭ ሆነዋል። ይህ ምሬት ለሥርዓት አልበኛ ወጣቶች ወንጀል መስፋፋት መንስኤ መሆኑንና ሁሉም ተፈናቃዮች የወንጀሉ ተባባሪ አለመሆናቸውን ይናገራሉ።
ተፈናቃዮቹ ‘’መንግስት ቃል የገባልንን በተግባር ይፈጽም። ኃላፊነት በመውሰድ ወደ መኖሪያ ቀያችን ይመልሱን። መንግስት እንደ ዜጋ ቆጥሮን ልጆቻችን መሰረታዊ የሆነውን የምግብ፣ የአልባሳት፣ የመጠለያና የሕክምና አገልግሎት ያቅርብልን። በስማችን የተሰበሰበውን የዘረፉ ሌቦች በሕግ ይጠየቁልን።’’ ሲሉ አቤቱታ አቅርበዋል።
ይህን ዜና እስካጠናቀርንበት ሰዓት ድረስ የከተማ ኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ቤተክርስቲያኑን ዙሪያውን ከበው ከጥቃት ለመከላከል በመጠባበቅ ላይ ናቸው።