ከሶማሊ ክልል ወደ ሃረር ከተማ የሚፈልሱ ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን ለከፍተኛ ችግሮች ተጋላጭ ሆነዋል
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 06 ቀን 2010 ዓ/ም ) ባለፈው ሳምንት በጂጂጋና አዋሳኝ ከተሞች የተፈጸመውን የጅምላ ጭፍጨፋና የተረፉ ለደኅንነታቸው በመስጋት ሕይወታቸን ለማዳን መኖሪያ ቀያቸውን እየተው የሚሰደዱ ዜጎች ቁጥራቸው እያሻቀበ ነው። ከሶማሊ ክልል ከሚሰደዱት ተፈናቃዮች ውስጥ ከፍተኛውን ቁጥር በማስተናገድ ሃረር ከተማ ቀዳሚዋ ሆናለች።
በሃረር ሸንኮር ወረዳ የከተማ ነዋሪዎችና በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ፍልሰተኞችን ተቀብለው እንክብካቤ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። አብዛሃኞቹ ባዶ እጃቸውን የወጡ በመሆናቸው ከክረምቱ ጋር ተያዞ የጤና ችግር ተጠቂ ሆነዋል። በጊዜያዊ መጠለያው ውስጥ ምንም ዓይነት የሕክምና አገልግሎት እንዳላገኙም ምንጮች ገልጸዋል።
የከተማ ነዋሪዎች የምግብ፣ የአልባሳትና ህመምተኞችን በመንከባከብ አጋርነታቸውን አሳይተዋል። በመንግስትም ሆነ በክልሉ መስተዳድር በኩል ወደ አዲስ አበባ ለሚሄዱት የመጓጓዣ አገልግሎት ከማቅረብ ውጭ ምንም ዓይነት ዕርዳታ ባለማግኘታቸው ማዘናቸውን ጉዳተኞቹ ቅሬታ አቅርበዋል።
ከተለያዩ የምስራቅ ኢትዮጵያ ክፍል በመፍለስ ወደ ሃረር ከተማ በአጠቃላይ 532 ስደተኞች ገብተዋል። ከእነዚህ ውስጥ 49 የሚሆኑት ታዳጊ ሕጻናቶች ሲሆኑ በከፋ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉም ታውቋል። 115ቱ ደግሞ በአሁኑ ወቅት በመጠለያ ውስጥ ይገኛሉ። እስካሁን ቁጥራቸው 417 የሚሆኑት ወደ አዲስ አበባ ተሸኝተዋል። በተለይም የሃረር ከተማ ወጣቶች ለተፈናቃዮቹ ለሚያደርጉላቸው እንክብካቤዎች ተጎጂዎቹ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።