የአፋር ነፃ አውጭ ግንባር መሪ ሱልጣን ሀንፈሬ አሊሚራህ ነገ ወደ አገራቸው ይገባሉ
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 06 ቀን 2010 ዓ/ም ) በሽግግር መንግስቱ ወቅት የአፋር ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት ሱልጣን ሀንፍሬ አሊ ሚራህ ኋላ ላይ በታናሽ ወንድማቸው በሀቢብ አሊ ሚራህ እንዲተኩ መደረጋቸው ይታወቃል።
የሱልጣን አሊ ሚራህ ልጆች ሀንፍሬ አሊ ሚራህ እና ሀቢብ አሊ ሚራህ በሽግግር መንግስቱ ወቅት ጉልህ አስተዋጽኦ ቢያደርጉም፤ ከ1987 ዓ.ም በኋላ ሕወሓት አዴት ተብሎ ከሚጠራውና ከትግራይ ክልል ጋር ድንበርተኛ ከሆነው ከዞን ሁለት አፋሮችን አምጥቶ በቦታቸው ላይ በመሾም ከስልጣን አውርዷቸዋል።
በዚህም ሳቢያ በአብዛኛው የአፋር ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ባላቸው በሱልጣን አሊ ሚራህ ቤተሰብ እና በኢህአዴግ አገዛዝ መካከል ኩርፊያ በመፈጠሩ፣ የአፋር ነጻነት ፓርቲን ሱልጣን ሀንፍሬ አሊ ሚራህን ጨምሮ ሌሎችም በትግሉ ተሳትፎ ሲያደርጉ የቆዩ አካላት ለስደት ተዳርገው ቆይተዋል።
ሱልጣን ሀንፍሬ በነገው ዕለት ወደ አፋር ክልል ሲገቡ በጣም ደማቅ አቀባበል እንደሚደረግላቸው ይጠበቃል። ሕዝቡ ዓደባባይ ወጥቶ ለመቀበል ከወዲሁ ዝግጅት እያደረገ ሲሆን፣ የሱልጣኑ ምስል ያለባቸው ካናቲራዎች እንደ ሚሌ፣ ሎግያ፣ ዱብቲ፣ አይሳኢታ እና ሰመራ በመሣሰሉ የተለያዩ የክልሉ ከተሞች እየተሸጡ ነው።
የአፋር ነጻነት ግንባር መሥራች የሆኑት የሀንፈሬ አባት ሱልጣን አሊ ሚራህ “እንኳን እኛና ግመሎቻችን የኢትዮጵያን ባንዲራ ያውቋታል” በሚለው አነጋገራቸው በአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ይታወቃሉ።