(ኢሳት ዲሲ–ነሐሴ 3/2010) በሰንደቅ የህትመትና የማስታወቂያ ድርጅት ላለፉት 14 ዓመት ያህል በየሳምንቱ ረቡዕ እየታተመ የሚወጣው “ሰንደቅ” ጋዜጣ ተዘጋ።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በአማርኛ ቋንቋ ታትመው ለገበያ የሚቀርቡ የግል ሳምንታዊ ጋዜጦችም “ሪፖርተር እና “አዲስ አድማስ” ብቻ ሆነዋል፡፡
ሰንደቅ ጋዜጣ የተዘጋው በየጊዜው እየናረ ከመጣው የሕትመት ዋጋ ጋር ተያይዞ ባጋጠመው ኪሳራ ምክንያት መሆኑን የሰንደቅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ፍሬው አበበ ገልጸዋል፡፡
ጋዜጣው በሳውዲ አረቢያ ታስረው በሚገኙት ሼህ አላሙዲን ይደገፍ እንደነበር ይነገራል።
ዋና አዘጋጁ ሰንደቅ ባለፉት ዓመታት በሥራ ላይ በቆየባቸው ዓመታት አንባቢዎቹን እና ደምበኞቹን አመስግኗል፡፡
ጋዜጣው ወደ 20 የሚደርሱ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞችን በትኗል፡፡
ሰንደቅ ጋዜጣ ከአቶ መለስ ሞት በኋላ ባለቤታቸው ወይዘሮ አዜብ መስፍን ቤተመንግስቱን በወቅቱ አለማስረከባቸውን ጠቅሶ መዘገቡ በወቅቱ ጉዳዩ አነጋጋሪ ሆኖ ዋና አዘጋጁም ለክስ ተዳርጎ ነበር።
የአቶ ጁነዲን ሳዶ ባለቤት ከሳዑዲ ኤምባሲ ጋር በተያያዘ በወንጀል ድርጊት ተጠርጥረው ስለመታሰራቸው ካወጣው ዜና ጋር ተያይዞ ሰፊና አነጋጋሪ አጀንዳ መፍጠሩም ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤቴክርስቲያን ፓትያርያክ አቡነ ማትያስ ላይ የቀረበ ትችት በማስተናገዱ የፓትርያኩን ስም አጥፍተሀል በሚል በቤተክህነት ክስ ቀርቦበት እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡