ትናንት በሚኒሶታ የተዘጋጀው የኢትዮጵያውያን መድረክ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን እና የአቶ ለማ መገርሳን የአመራር ብቃት ያመላከተ ነው ሲሉ በርካታ ኢትዮጵያውያን ገለጹ።
( ኢሳት ዜና ሃምሌ 24 ቀን 2010 ዓ/ም )19 ሺህ ኢትዮጵያውያን የታደሙበት የሚኒሶታው መድረክ ህብረብሄራዊነትን በማንጸባረቅ በኩል ልዩ ውበት የታዪበትን ያህል ፣መድረኩን ያስተባብሩ የነበሩ ጥቂት ሰዎች ዝግጁቱን ወደ ውጥረት የወሰዱት ገና የክብር እንግዶቹ ወደ ስፍራው ሳይደርሱ ነው።
ከጥቂት ጊዜ በፊት የህወኃት አመራሮች አማራና ኦሮሞን “እሳትና ጭድ” በማለት በፖለቲካ አብረው እንደማይቆሙ ቢናገሩም፣በሁሉም ወገን ወደ ጫፍ ከወጡ ጥቂት ሰዎች በስተቀር አብዛኛው ሕዝብ ልብ ለልብ የተሣሰሩ መኮኑን፤ የትናንቱ የሚኒሶታ መድረክ ተጨማሪ ምስክር ሆኖ ማለፉን ብዙዎች ይናገራሉ።
አብዛኛው የዝግጅቱ ታዳሚ በኦሮሚኛ፣ በአማርኛ፣ በጉራጊኛ፣ በትግርኛ፣በሶማሊኛና በተለያዩ ቋንቋዎች በደስታ እየተጫዎተና ስሜቱን እየገለጸ መቆዬቱ መድረኩን ለተቆጣጠሩት ጥቂት ሰዎች ምቾት እንዳልሰጠ በስፍራው የተገኙ ምስክሮችና ጋዜጠኞች ገልጸዋል።
ጋዜጠኛ ሄኖክ አለማየሁ ከዝግጅቱ ቦታ ባጠናቀረው ሪፖርት የኢትዮጵያ ባንዲራን የያዙ ተወዛዋዦችን ከመድረክ ከመግፋት ጀምሮ ሌሎችንም ተንኮሎችን በመፈጸም አጠቃላይ መድረኩን ወደ ውጥረት የወሰዱትን ልጆች በቅርብ እንደሚያውቃቸው ገልጿል።
፦“ይህን ያደረጉት ልጆችን አውቃቸዋለሁ፤ የአብይና የለማ ደጋፊዎች አይደሉም:: በፌስቡካቸው ለማንም፣ አብይንም ሲቃወሙ የከረሙ ናቸው:: ሆን ብለው አብዛኛውን ሕዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር ሊያለያዩ ተልዕኮ ያላቸው የፖለቲካ ነጋዴዎች ናቸው:: በኋላ ላይ ለማና አብይ ስለኢትዮጵያዊነት የተናገሩትንና የሕዝቡን የአንድነት ስሜት ከተመለከቱ በኋላ በኪሳራ ስሜት አቀርቅረው አይቻቸዋለሁ”ብሏል።
“ዶክተር አብይም ሲደረግ የነበረውን አሻጥር በዐይናቸው ስላዩና ስለታዘቡ ነው “የአማራ ባህላዊ ሙዚቃ ባለመጫወቱ ይቅርታ” የጠየቁት” ያለው ጋዜጠኛ ሄኖክ፣ እድሜ ለአቶ ለማ እና ለዶክተር አብይ የበሰለ አመራር ጥቂት ተንኮለኞች ወገኖች በመጨረሻም ላይ አፍረው ሄደዋል”ብሏል።
እነዚህ በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች አቶ ለማ መገርሳ ንግግር ማድረክ ሲጀምሩ “ለምን በአማርኛ ይናገራሉ?”በማለት ሊያቋርጧቸው የሞከሩ ቢሆንም ፤ አቶ ለማ እጅግ በተጋጋ መንፈስ እና ብስለት በተሞላበት ሁኔታ ተቃዋሚዎቹን ጸጥ በማሰኘት ንግግራቸውን ቀጥለዋል።
“የኢትዮጵያ ልጆች ዘር፣ ቀለም፣ ሀይማኖት ሳይገድበን እንዲህ በአማረ መልኩ በመገናኘታችን እንኳን ደስ አለን” በማለት ንግግራቸውን የጀመሩት አቶ ለማ መገርሳ ፤ “ይህ አንድነታችን እንዲጠበቅ የምንለፋው፣ የምንጸልዬው፣ የምንዋትተውና የምንቃትተው ለውበታችን እና ለማማራችን ብቻ ሳይሖን ከመለያዬት እና ከመጠጣጠል ውርደትና ሽንፈት እንጂ ምንም ጥቅም እንደማይገኝ ስለተገነዘብን ነው”ብለዋል።
“አገራችሁ የናፈቀቻችሁ እናንተም ሀገራችሁን የናፈቃችሁ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ፣ ሀገራችን ኢትዮጵያ ይበልጥ እንድታድግና እንድትጠነክር ከፈለግን አንዳችን ከአንዳችን መደመር፣አንዳችን ለአንዳችን ማሰብ፣አንድነታችንን ማጠናከር ይገባናል ብለዋል።
ኦቦ ለማ አክለውም፦“ኦሮሞነት ለኢትዮጵያ ስጋት ሳይሆን ውበት ነው።አቅም ነው።ኡልበት ነው።ሀብት ነው።አማራነት ለኢትዮጵያ ስጋት ሳይሆን ተጨማሪ ኃይልና ጉልበት ነው።ሶማሌነት ለኢትዮጵያ ስጋት ሳይሖን ውበት ነው።ኃይልና ጉልበት ነው።መላው የሀገራችን ሕዝቦች ለኢትዮጵያ ስጋቶች ሳንሆን ውበቶች ነን።ኃይሎች ነን።ጉልበቶች ነን።”ሲሉም ተናግረዋል።
በውጭ ሀገራት ተወልደው ያደጉ ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ሀገራዊ የባህል ጭፈራዎች ማሳዬታቸውን ያደነቁት አቶ ለማ መገርሳ፦”ይህ ማለት የትም ብንርቅ እኛ ኢትዮጵያውያን ሀገራችንን እንደማንረሳ የሚያመላክት ነው።ታዲያ ይህን ላዬ እውነት ኢትዮጵያዊነት ሱስ አይደለምን?” ሲሉ በአግራሞት ጠይቀዋል።
በመሆኑም እኛ የኢትዮጵያ ልጆች አንድ ሆነን ሀገራችንን እንለውጣት ሲሉ አቶ ለማ ጥሪ አቅርበዋል።
ተከታዩ ተናጋሪ ጠቅላይ፡ሚኒስትር አብይ አሕመድ ሲሆኑ ንግግራቸውን ከመጀመራቸው በፊት መድረክ ላይ ውዝዋዜ ያቀረቡት ልጆች ሌሎች ባህሎችን አሳይተው የአማራን ባህል አለማሳዬታቸውን በማጤን ፣ ልጆቹ ለፈጠሩት ስህተት ይቅርታ ጠይቀዋል።
ምክንያቱም እንደ ዶክተር አብይ ገለጻ ፣ ታዳጊ ሕጻናቱ የዚያን ሁሉ ባህል አሳይተው አንድ ቢዘነጉ ኃላፊነት የሚወስዱት ልጆቹ ሳይሆኑ እኛ ትልልቆቹ ነን።
“ላለፉት በርካታ አመታት ያላስተማርናቸውን፣ ያላሳዬናቸውን እና ያልነገርናቸውን በአንድ ጀምበር እንዴት ሊያጡት ይችላሉ?”ያሉት ዶክተር አብይ “በዚህ ምክንያት ልጆቻችን ተቀራርበው ወደማይነጋገሩበትና ተነጋግረው ወደማይግባቡበት የባዕድነትና የጠላትነት ደረጃ ላይ አድርሰናቸው ስለቆየን ኃላፊነት መውሰድ ብቻ ሳይሆን ቀን ከሌት ተደምረን ልንሰራ ይገባናል” ብለዋል።
በመካከላችን የተገነባው የጥላቻ ግንብ አድጎ ሌላውን ብቻ ሳይሆን የምንወዳት ሀገራችንን እና የነገ ዕጣ ፈንታችንን ጋርዶብናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ባሳለፍነው የመጠላላት መንገድ ማንም ተጠቃሚ እንደማይሆን ከታሪክ ተምረን ፍቅርን በመዝራት እና ይቅር በመባባል ለአፍሪካ ጭምር ትሩፋት የምትሆን አንዲት ታላቅ ኢትዮጵያን መገንባት እንደምንችል ለዓለም ማሳዬት ይኖርብናል ብለዋል።
እናም ከትናንት በስቲያ በዋሽንግተን፣ ትናንት በሎሳንጀለስ የጥላቻ ግንቦች አፈራርሰና ል ያሉት ዶክተር አብይ፣ ለሚኒሶታ ያለኝ ግብዣ “ፍርስራሹን በጋራ እናጽዳ “የሚል ነው ብለዋል።
የለውጡ ኃይል መሪ ሃሳብ “ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገባ” የሚል እንደሆነ ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ መሪ ሀሳብ መሰረት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገራት በተለያዩ ምክንያቶች የተነጣጠሉ ኢትዮጵያውያንን በአንድነትና በህብረት ማቆሙ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።