‹ከእኔ ክስና እስራት በስተጀርባ በመንግሥት ውስጥ ጡንቻቸው የጠነከረ ማፊያዎች ነበሩ›› ሲሉ የቀድሞው የገቢዎች ሚኒስትር ገለጹ።
( ኢሳት ዜና ሃምሌ 23 ቀን 2010 ዓ/ም ) የቀድሞ ሚኒስትር አቶ መላኩ ፋንታ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በሙስና ሰበብ ለእስር የተዳረጉት የአሠራር ስህተቶችን ሲያዩ በመቃወማቸውና ሹመኞችን ሙስና አላስበላም በማለታቸው እንደሆነ በስፋት ዘርዝረዋል።
በአቶ በረከት ስምኦን ባለቤት ስም ከውጭ አገር የገባ የፊልም ካሜራ እንዲወረስ ትዕዛዝ ስለመስጠታቸው እና ይኼ የሆነው ከአቶ በረከት ጋር በተለያዩ ምክንያቶች በነበራቸው ግጭት ምክንያት እንደሆነ ስለሚወራው ነገር ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ መላኩ፦”ልክ ነው፡፡ በአቶ በረከት ባለቤት ስም ዘመናዊ የፊልም ካሜራ ገብቶ ተይዟል” በማለት ነው ምላሽ መስጠት የጀመሩት።
“የጉምሩክ ሠራተኞች ‹‹የአቶ በረከት ባለቤት ዕቃ ነው›› ሲሉኝ፣ ‹‹ይሁና እንደ ማንኛውም ዜጋ መስተናገድ አለባቸው›› ብያለሁ” የሚሉት የቀድሞው የገቢዎች ሚኒስትር፣ “ታክስና ቀረጡን መክፈል ከቻሉ ማውጣት እንደሚችሉ ካልከፈሉ ግን ዕቃው መወረስ አለበት ብለው ትእ ዛዝ በመስጠታቸው ዕቃው መወረሱን ገልጸዋል፡፡
“ይኼንን ያደረግኩት ከአቶ በረከት ጋር ግጭት ወይም ጥላቻ ስላለኝ ሳይሖን በቦታው የተቀመጥኩት ሕግ ለማስከበር በመሆኑ ነው”የሚሉት አቶ መላኩ ፋንታ፤ “አቶ በረከት ግን በእኔ ለይ ጥላቻ እያደረባቸው የመጣ ይመስለኛል፡፡ ይኼንንም በሚመለከት በብአዴን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ፊት አንስቼ ግምገማ ተካሂዶበታል”ብለዋል።
እንዲሁም አቶ በረከት መጽሐፋቸውን ውጭ አገር አሳትመው ወደ አገር ውስጥ ከገባ በኋላ ወደ ውጭ ለመሸጥ ሲፈልጉ ፦‹‹አሠራሩን ተከተሉ›› ብላቸውም ግን ያንን አላደረጉም ያሉት የቀድሞው የገቢዎች ሚኒስትር፤ “መጽሐፉ በተለያየ መንገድ ወጥቶ እንዲሸጥ ከመደረጉም በላይ የግምገማው መድረክ እርሳቸውን ማጥቂያና ቂም መወጫ ሆኖ መጠናቀቁን አውስተዋል።
ይህ ጣልቃ ገብነትም እየባሰና ሕገወጥ ሥራዎች እየበረከቱ የመጣው በተለይ ከአቶ መለስ ሞት በኋላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“ጉዳዩን ለተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም አላስረዷቸውም?”ወይ፡ተብለው በጋዜጣው የተጠየቁት አቶ መላኩ ፋንታ
“አስረድቻቸዋለሁ፡፡ እነ ማን በምን ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ እንደሆነ ስነግራቸው ‹‹እኔም አውቀዋለሁ›› ብለውኛል”ሲሉ መልሰዋል።
“ ከቡድኑ አባላት ውስጥ አንዳንዶቹን እቀርባቸው ስለነበር የሚያደርጉትን ጣልቃ ገብነት እንዲያቆሙ በምክር መልክም ነግሬያቸው ነበር” ያሉት አቶ መላኩ፤ “ይሁንና እየሆነ ያለው ነገር ለኢሕአዴግም ጥሩ አይደለም ብዬ በመምከሬ ተመልሰው ለእኔ ጠላት ሆኑኝ”ብለዋል።
“ሦስት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከአንድ ድርጅት ሆነው በእኔ ላይ ውሳኔ ሲያሳልፉ ለብአዴን ደግሞ ሌላኛው የቡድኑ አባል አስተላለፈ”ያሉት የቀድሞው ሚኒስትር፤ “ጉዳዩን ለአቶ ኃይለ ማርያም ሳስረዳቸው ‹‹አውቃለሁ፡፡ ጉሮሮአቸው ላይ ስለቆምክ ነው፡፡ ቢሆንም ከጎንህ እኔ ስላለሁ ሥራህን ቀጥል…›› ብለውኝ ነበር”ሲሉ ገልጸዋል።
“አሁንም ይፋ የወጣውን በተለያየ የልማት ሴክተር ይደረግ የነበረውን ዝርፊያ አስቀድሜ ለአቶ ኃይለማርያም ነገሬያቸው ነበር፡፡ ይሁንና በግልባጩ ወሬው እየወጣ ለእኔ መምቻ ነው የሆነው”ሲሉም አክለዋል።
ሥራዬ ሕግን ማስከበር ስለነበር በተመሳሳይ ኤፈርትና ጥረት ወደ ታክስ ሲስተም እንዲገቡ እና ብድራቸውንም እንዲከፍሉ ብዙ መንገድ ተጉዣለሁ ያሉት አቶ መላኩ፣ በዚህ አጋጣሚ አቶ ዮሴፍ ረታ የጥረት ድርጅቶች ወደ ታክስ ሲስተሙ እንዲገቡ ብዙ ጥረት በማድረጉ ላመሰግነው እፈልጋለሁ ብለዋል።
እነዚህና ሌሎች ልዩነቶች እነዚህ ሲደመሩ ‹‹ሌላ የፖለቲካ አመለካከት አለው›› ተብለው መፈረጃቸውን እና ለእስር መብቃታቸውን አስረድተዋል።
አቶ ገዱ አንዳርጋቻው ሲናገሩ ‹‹ያልታደሱ የአሮጌው ዘመን ቁማርተኞች›› ያሏቸው አሉ ያሉት አቶ መላኩ ፋንታ፤ “በእኔ እምነት ያልታደሱ ሳይሆን ፈጽሞ መታደስ የማይችሉም አሉ ብለዋል።