(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 20/2010) የኢንጅነር ስመኘው በቀለ ግድያ በአስቸኳይ ተጣርቶ ፍትህ እንዲሰጥ በጎንደር ፣ ማክሰኝትና በባህርዳር ከተሞች የሚገኙ ወጣቶች ጠየቁ።
በጎንደር በነበረው ህዝባዊ ቁጣ ከጸጥታ አስከባሪዎች ጋር ግጭት ተፈጥሮ አንድ ወጣትና አንድ ታዳጊ በጥይት ተመተው ጉዳት ደርሶባቸዋል።
የኢንጅነር ስመኘው በቀለ የቀብር ስነስርዓት የፊታችን እሁድ በአዲስ አበባ ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን እንደሚፈጸም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ትላንት ጠዋት አዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ተገድለው የተገኙት የአባይ ግድብ ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ስመኘው በቀለ ጉዳይ በመላው ዓለም በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ብርቱ ሀዝን ፈጥሯል።
በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር እንደተገለጸውም ኢንጂነር ስመኘው በቀለ በጥይት ተመትው ህይወታቸው አልፏል።
ምርመራው ገና በሂደት ላይ ቢሆንም ድርጊቱ የግድያ እርምጃ መሆኑን በመጥቀስ በተለያዩ አከባቢዎች ቁጣ ተቀስቅሷል።
ቁጣው ወደ ሰላም መደፍረስ እንዳያመራ ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ከየአቅጣጫው መልዕክቶች እየተላለፉ ነው።
ዜናው እንደተሰማ በተለይ በአዲስ አበባ ና ጎንደር ተቃውሞ የተቀሰቀሰ ሲሆን በኢንጅነር ስመኘው የትውልድ ቦታ ማክሰኝትም ህዝቡ አስቸኳይ ምርመራ ተደርጎ ውጤቱ ይገልጽ ሲል ጥያቄ አቅርቧል።
ወጣቶች ተሰባስበው ፍትህ እንዲሰጣቸውና ገዳዩች እንዲያዙ በመጠየቅ መሪር ሀዘናቸውን አሰምተዋል።
ዛሬ ማንነቱ ባልታወቀ አካል በጎንደር የተጠራ ተቃውሞ ግጭት አስከትሎ አንድ ወጣት በጥይት መመታቱን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
በትላንትናው ዕለት በጎንደር የሰላም ባስ አውቶብስ መቃጠልና ሁሌታውን ወደ ለየለት ትርምስ ለመለወጥ የሚንቀሳቀስ ሃይል በመኖሩ ህዝቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ እየተጠየቀ ነው።
በጎንደር ወደ አደባባይ የወጣው ህዝብ ወደ ግጭት እንዳይገባ በሀገር ሽማግሌዎች በተላለፈ መልዕክት ሁሉም ወደ ቤቱ እንዲበተን መደረጉን ለማወቅ ተችሏል።
ወጣቱ በዚህ ቁጭት ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እንዳይሄድ በተለይም እየታየ ያለውን የለውጥ ሂደት የሚቀለብስ እርምጃ እንዳይወስድ ስሜቱን እንዲቆጣጠር መልዕክቶች ከተለያዩ አከባቢዎች እየተላለፉ ነው።
በባህርዳር ወጣቶች በቀበሌ 04 ድንኳን ጥለው ሀዘናቸውን እየገለፁ ሲሆን ፍትህ ለኢንጅነር ስመኘው በቀለ የሚል መልዕክት በማሰማት ምርመራው በአፋጣኝ ተጠናቆ ውጤቱ እንዲታወቅ ጠይቀዋል።
በአዲስ አበባም በኢንጅነር ስመኘው መኖሪያ ቤት የሀዘን ፕሮግራም በመካሄድ ላይ መሆኑ ታውቋል። የኢንጅነር ስመኘው ወላጅ አባት ከጎንደር አዲስ አበባ መግባታቸም ተገልጿል።
በሌላ በኩል የኢንጅነር ስመኘው በቀለ የቀብር ስነስርዓት የፊታችን እሁድ እንደሚፈጸም ለማወቅ ተችሏል።
በመንግስት በኩል የቀብር ስነስርዓቱን ለታላላቅ ሰዎች በሚሰጥ ተገቢ ክብር እንደሚፈጸምም ታውቋል።
በአዲስ አበባ በቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን እንደሚፈጽም የወጣው መረሃ ግብር ያሳያል።