የደቡብ ሱዳን 400 የፓርላማ አባላት ቅንጡ መኪና እንዲገዙ ለእያንዳንዳቸው 40 ሺህ ዶላር በብድር መልክ መሰጠቱ ህዝባዊ ቁጣ አስነሳ።

የደቡብ ሱዳን 400 የፓርላማ አባላት ቅንጡ መኪና እንዲገዙ ለእያንዳንዳቸው 40 ሺህ ዶላር በብድር መልክ መሰጠቱ ህዝባዊ ቁጣ አስነሳ።
( ኢሳት ዜና ሃምሌ 19 ቀን 2010 ዓ/ም ) ቢቢሲ እንደዘገበው የሳልቫኪር መንግስት አጠቃላይ ለፓርላማ አባላቱ መኪና መግዣ 16 ሚሊዮን ዶላር ነው ያወጣው።
የፕሬዚዳንቱ ቃል አቀባይ “የፓርላማ አባሎቻችን ሞተር ባይስክል መጠቀም የለባቸውም” በማለት ውሳኔው ትክክል እንደሆነ ለመከላከል ሞክረዋል።
የፓርላማ አባላቱ የሳልቫኪር የሥልጣን ዘመን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር እስከ 2021 ድረስ እንዲራዘም ከሁለት ሳምንት በፊት ድምጽ መስጠታቸውን ያስታወሱ የሀገሩ ነዋሪዎች፣ “ከደሀ ሀገር ላይ ለመኪና መግዣ ተብሎ ይህን ያህል መሰጠቱ፤ ለዚያ ውለታቸው እንደ ሽልማት ነው” ብለዋል። የጁባ መንግስት በሀገሪቱ እየቀጠለ ባለው ጦርነት ሳቢያ ምርጫ እንደማይኖርማስታወቁ ይታወሳል።
በ2013 በሳል ቫኪር እና በምክትላቸው በሪክ ማቻር መካከል በተቀሰቀሰውና እስካሁን መቋጫ ባልተገኘለት ጦርነት ሳቢያ፣ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የደቡብ ሱዳን ሕዝቦች በከፍተኛ የምግብ እጥረት ተጠቂዎች መሆናቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በዓለም የምግብ ፕሮግራም ሪፖርት መሰረት በጦርነቱ ሳቢያ 3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ደቡብ ሱዳናውያን ቤታቸውን ጥለው ተሰደዋል።