(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 18/2010)የደቡብ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ደሴ ዳልኬ ከስልጣናቸው ወረዱ።
በምትካቸው የቀድሞ የሲዳማ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሚሊዮን ማቲዮስ የክልሉ ፕሬዝዳንት ሆነው ትላንት ተመርጠዋል።
በቅርቡ በሐዋሳ ከተማ ከተካሄደው ግጭት ጋር ተያይዞ ወደ አካባቢው የተጓዙት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የአካባቢው ባለስልጣናት በፈቃደኝነት ስልጣን እንዲለቁ መጠየቃቸው ይታወሳል።
በሐዋሳና በወላይታ ሶዶ ከተማ በተከታታይ ቀናት የተካሄዱትን ግጭቶች ተከትሎ የሲዳማ ዞን አስተዳዳሪና የሃዋሳ ከተማ ከንቲባ እንዲሁም የወላይታ ዞን አስተዳደርና ሌሎች ባለስልጣናት በፈቃዳቸውና በግፊት ከስልጣን መነሳታቸውም አይዘነጋም።
ማክሰኞ ሐምሌ 17/2010 ሃዋሳ ላይ በተካሄደው የደቡብ ክልል ምክር ቤት 7ኛ መደበኛ ጉባኤም አቶ ደሴ ዳልኬን ተክተው የክልሉ ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ የተጠቆሙትን አቶ ሚሊዮን ማቲዎስን ምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ እንደመረጣቸው የክልሉ መንግስት አስታውቋል።
አቶ ሚሊዮን ማቲዮስ አቶ ሲራጅ ፈርጌሳን ተክተው የደኢሕዴን ምክትል ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት ከወር በፊት ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ከፍተኛ የስልጣን ብወዛ የተካሄደበት የደቡብ ክልል መሆኑ ይታወቃል።
ርምጃው በደኢሕዴን ውስጥ ያሉትን የሕወሃት ወኪሎች የማጥራትና ክልሉን ከአገልጋይነት ነጻ የማውጣት ርምጃ እንደሆነም ተመልክቷል።
የደኢሕዴን ሊቀመንበር አቶ ሽፈራው ሽጉጤና ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ ይህንን የያዙትን ስልጣን ከሶስት ወራት በላይ ሳይጓዙበት መነሳታቸው ይታወሳል።