የኪነጥበብ ባለሙያዎች ለኢትዮጵያና ኤርትራ ግኑኝነት እንሰራለን አሉ

(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 18/2010)በቅርቡ ወደ ኤርትራ የተጓዙት የኢትዮጵያ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ለኢትዮጵያና ኤርትራ ግኑኝነት መጠናከር በሙያቸው የራሳቸውን አስተዋጾ እንደሚያደርጉ አስታወቁ።

አስመራ ላይ ከኢሳት ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት  አራት ታዋቂ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ይህ ሁኔታ እንዲፈጠር  አስተዋጾ ላደረጉት  ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ  ምስጋና አቅርበዋል።

የኪነጥበብ ባለሙያዎቹን አብርሃም ወልዴን ፣መስፍን ጌታቸውን፣ሰለሞን ቦጋለንና ሳምሶን ታደሰን በማነጋገር ጠይብ  ቃዲ  ከአስመራ ያጠናቀረውን ሪፖርት ብሩታዊት ግርማዬ ታቀርበዋለች።

ከሁለት አስርት አመታት በላይ ተቋርጦ የነበረውና ባለፈው ሳምንት በጀመረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመጀመሪያ በረራ ከተጓዙት የኪነጥበብ ባለሙያዎች መካከል መስፍን ጌታቸው፣ ሰለሞን ቦጋለ፣አብርሃም ወልዴ  እና ሳምሶን ታደሰ ይገኙበታል።
ኢሳት ያነጋገራቸው እነዚህ አርቲስቶች በኢትዮጵያና በኤርትራ ህዝብና መንግስት መካከል በአዲስ መልክ የተጀመረው ግንኙነት እንዲጠናከር እነርሱም በሙያቸው አስተዋጻኦ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

በኢትዮጲያ በባላገሩ ሾውና ሌሎች የኪነጥበብ ስራዎቹ የሚታወቀውና አስመራን ለመጀመሪያ ጊዜ የጎበኘው አርቲስት አብርሃም ወልዴ የአስመራ ህዝብ ያሳየን ፍቅር የተለየ ነው ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል።
“ሰው ለሰው” እና   “ዘመን” በተባሉ የቴሊቪዥ ድራማ  ድርሰቶቹ የሚታወቀው  አርቲስት መስፍን ጌታቸው በበኩሉ በቅድሚያ ከኢትዮጲያ ሳተላይ ቴሌቪዥን (ኢሳት) ጋር በነፃነት ቃለምልልስ ለማድረግ ሁኔታው በመፍቀዱ የተሰማውን ደስታ ገልጿል።

በኢሳት እና በአርበኞች ግንቦት ሰባት መሪዎች ስለ ኤርትራ ይሰጥ የነበረውን ምስክርነት በማየት ማመኑን አመልክቷል።
መንግስት ከመንግስት ጋር ሊጣላ ይችላል ነገር ግን የመንግስታቱ ጸብ  ዳግመኛ ወደ ህዝብ እንዳይወርድ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል  ሲሉም ተናግረዋል የኪነጥበብ ባለሙያዎቹ።

የኪነጥበብ ባለሙያዎቹ  ዶክተር አብይ አህመድና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ይሄን አዲስ እድል ስለፈጠሩም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

አሁን በዶክተር አብይ አህመድ የተጀመረው የመደመር እሴትና ባህል ከ27 አመታት በፊት ተደርጎ ቢሆን መልካም ነበር ብለዋል የኪነጥበብ ባለሙያዎቹ።

ብዙ ስህተቶችን ከመስራትም እንድን ነበር አሁንም ቢሆን ግን አልዘገየንም ዶክተር አብይን በመደገፍ ማበረታታት ይገባናል  ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።