የጌዲዮ ማህበረሰብ አባላት ለደረሰባቸው ጥቃት አስፈላጊው ካሳ እንዲከፈላቸውና ጥያቄያቸውም እንዲመለስላቸው ጠየቁ
( ኢሳት ዜና ሃምሌ 18 ቀን 2010 ዓ/ም ) የማህበረሰቡ ተወካዮች ለጠ/ሚኒስትሩ በጻፉት ደብዳቤ ዘንድሮም ሆነ ከዚህ ቀደም በተነሳው ጥያቄ ምክንያት ለአመታት ለተፈጸመው የሰው እልቂት ለሟች ቤተሰቦች የደም ካሳ እንዲከፈል ጠይቀዋል።
“በዘንድሮው እልቂት፣ በተቋማትና ንብረት መውደም መንስኤ የሆኑ ንጹሃንን በማደናገር አሳስተው አሰለፉ፣ ጥፋትና ውድመት ያደረሱ ያደረሱ በየደረጃው ያሉ አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡም” ጠይቀዋል።
የማህበረሰቡ ተወላጆች በም/ል ጠ/ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ በኦሮምያ ክልል ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂምና ሌሎችም ባለስልጣናት ወደ አካባቢው በመጓዝ ለችግሩ መፍረትሄ እንደሚሰጡ የተናገሩ ቢሆንም፣ አሁንም ችግሩ አለመቆሙን ደብዳቤው ይገልጻል። አሁንም ድረስ በምዕራብና ምስራቅ ጉጂ ዞኖች ልዩ ልዩ ተቋማት ውስጥ የጌዲዮ ተወላጆች ተጠልለው ወደ ሚገኙበት ጣቢያ በመግባት ዝርፊያና ሁከት የሚፈጽሙ፣ ሴቶቻቸውን የሚደፍሩ ሰዎች መኖራቸውን፣ በመጠለያ ጣቢያ የሚቀርበው ሰብአዊ ድጋፍ በቂ ባለመሆኑ ወደ ውጭ ወጥተው ህይወታቸውን ለማቆየት የሚሞክሩ ሰዎች ህይወታቸውን እያጡ መሆኑን ተወላጆቹ በደብዳቤያቸው ገልጸዋል።
የማህበረሰቡ ተወላጆች ጥያቄያቸው በህይወት የመኖርና ያለመኖር የዋስትና ጥያቄ መሆኑን ገልጸው፣ ላነሱዋቸው ጥያቄዎች መንግስት አፋጣኝ መልስ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።