በደሴ ከተማ ሸዋ በር መስጂድ ውስጥ ጥቃት ያደረሱ ተጠርጣሪዎች ተያዙ።

በደሴ ከተማ ሸዋ በር መስጂድ ውስጥ ጥቃት ያደረሱ ተጠርጣሪዎች ተያዙ።
( ኢሳት ዜና ሃምሌ 17 ቀን 2010 ዓ/ም ) በትናንትናው እለት በደሴ ከተማ ሸዋ በር በመባል በሚጠራው መስጂድ ውስጥ ድምጽ አልባ የስለት መሳሪዎችን ይዘው በመግባት መስኪዱ ውስጥ የነበሩ ምእመናን ላይ ጉዳት አድርሰዋል። በመስጅዱ ሃይማኖታዊ ፀሎት በማድረግ ላይ እያሉ ቁርአን እናስቀራለን በሚሉና አናስቀራም በሚሉ መሃከል አለመግባባት መፈጠሩን ምንጮቻችን ገልጸዋል።
በወቅቱ በተከሠተው ግጭት በ11 ሰላማዊ ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል። ጉዳተኞቹ በደሴ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ሲሆን ከተጎዱት ውስጥ አንድ ሰው ከባድ ጉዳት የደረሰበት ሲሆን፣ 3 መካከለኛና 7ቱ ደግሞ ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል። የሆስፒታሉ ሜዴካል ዳይሪክተር ዶክተር መንግስቱ ወርቁ ጉዳተኞቹ በሆስፒታሉ ድንገተኛ አደጋ ክፍል አስፈላጊውን ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑንና እስካሁን የሞተ ሰው አለመኖሩን አስታውቀዋል።
በፀጥታ ኃይሉና በሕብረተሰብቡ ትብብርና ከትትል እስካሁን 59 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው በፖሊስ ምርመራ እየተደረገላቸው መሆኑም ታውቋል።
በዛሬው እለት ሙስሊሙ መኅበረሰብ የችግሩን ምንጭ ለማወቅና እልባት ለመስጠት ባደረጉት ስብሰባ ችግሩ ከቀድሞ የኮሚቴ አባላትና የከተማው አስተዳደር ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልጸዋል። በተጨማሪም ጥቃቱን አድራሾች የአካባቢው ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የመጡና የውጭ ዜጎችም መኖራቸውንና ይህም ከጀርባው የሌሎች እጅ ሳይኖርበት አይቀርም ተብሏል።