ሕገ ወጥ የመሳሪያና የገንዘብ ዝውውር እየጨመረ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 16/2010) በኢትዮጵያ ሕገ ወጥ የመሳሪያና የገንዘብ ዝውውር እየጨመረ መምጣቱ ተገለጸ።

ይህ በሃገሪቱ ሰላምና ኢኮኖሚ ላይ ተጽእኖ ለማድረግ ያለመ ስለመሆኑም የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

የጦር መሳሪያዎቹ ከቱርክ ተነስተው በሱዳንና በጅቡቲ በኩል እየገቡ መሆናቸውንም ከኮሚሽነሩ መግለጫ መረዳት ተችሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በጥቁር ገበያና በመደበኛ የሚመነዘረው የውጭ ገንዘብ ምንዛሪ ተቀራራቢ ደረጃ ላይ መድረሳቸው ታወቋል።

በዶላር እስከ 10 ብር የነበረው ልዩነት ወደ ሳንቲም ደረጃ መውረዱ ተመልክቷል።

በሳምንቱ መጨረሻ 10 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወር በቁጥጥር ስር መዋሉን ነው የፌደራል ፖሊስ ያስታወቀው።

በተመሳሳይ ሕገ ወጥ የመሳሪያ ዝውውሩ የቀጠለ ሲሆን ፌደራል ፖሊስ ከአዲስ አበባና ከኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ጋር በመሆን በአዲስ አበባ አቅራቢያ ባካሄዱት ክትትል ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችንም ሆነ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውሩን በመቆጣጠር ላይ መሆናቸው ተመልክቷል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ዘይኑ ጀማል ለመገናኛ ብዙሃን እንደገለጹት ከመሳሪያው ባሻገር የተያዙት የክላሽና የሽጉጥ ጥይቶች 80ሺ ደርሰዋል።

መሳሪዎቹ ከቱርክ ተነስተው በጅቡቲና በሱዳን በኩል እየገቡ መሆናቸውንም አመልክተዋል።

በተመሳሳይ ዜና ከአዲስ አበባ ወደ ጅጅጋ ሲጓዝ የነበረ 70ሺ የአሜሪካን ዶላር ምስራቅ ሸዋ ላይ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልጿል።

በድንበር አካባቢ ቶጎ ውጫሌ ኬላ ላይ ደግሞ የአሜሪካን ዶላርና የኢትዮጵያን ብር ጨምሮ የተለያዩ ሃገራት ገንዘቦች መያዛቸው ተዘግቧል።

ከጦር መሳሪያና ከሕገወጥ ገንዘብ ዝውውሩ ጋር በተያያዘ 18 ያህል ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ከአፋር ሰመራ ቅርንጫፍ ወደ ደሴ ሲያጓጉዝ የነበረው 24 ሚሊየን ብር በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል።

ባንኩ ገንዘቡ ሲጓጓዝ የነበረው ደሴ ወደሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለማስገባት ነው በማለት ገንዘቡ እንዲለቀቅለት ጠይቋል።