(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 11/2010) በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ይፋ የተደረገው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።
ትረስት ፈንዱ እያንዳንዱ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ በቀን 1 ዶላርና እንደ አቅሙ ለሃገሩ አስተዋጽኦ የሚያደርግበት አሰራር ነው።
ለዚሁም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሂሳብ ቁጥር ተከፍቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለዲያስፖራው ያቀረቡትን የድጋፍ ጥሪ መነሻ በማድረግ የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ትረስት ፈንድ ተቋቁሟል።
በዚሁም መሰረት የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ትረስት ፈንድ በንግድ ባንክ ሂሳብ ቁጥር ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ነው የተገለጸው።
ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በመስራት ላይ የሚገኙ የውጭ ሃገር ገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶችም ይፋ ተደርገዋል።
ለዚሁ ስራም የትረስት ፈንዱ ድረገጽ እንደሚዘጋጅና በመላው አለም የሚገኙ የዲያስፖራው አባላት ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ሁኔታዎች መመቻቸታቸው ተገለጿል።
በኢትዮጵያ ትረስት ፈንድ የሚሰበሰበው ገንዘብ በሃገሪቱ ያለውን የውጭ ምንዛሪ ችግር ከመቅረፍ በተጨማሪ ለልዩ ልዩ የልማት ስራዎች እንደሚውል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ መናገራቸው ይታወሳል።
ዶክተር አብይ በወቅቱ እንዳሉት በተለያዩ የአለም አካባቢዎች የሚገኙ 1 ሚሊየን የዲያስፖራ አባላት በየቀኑ አንድ ዶላር ቢያወጡ በየወሩ 30 ሚሊየን ዶላር ማግኘት ይቻላል።
ይህ ማለት በየቀኑ በየአካባቢው አንድ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወይንም ጤና ጣቢያ መገንባት ይቻላል።
በኢትዮጵያ የዲያስፖራ ትረስት ፈንድ የተከፈተውን የንግድ ባንክ ቁጥር በድረገጽ ላይ መስፈሩንና በገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች በኩል ማግኘት እንደሚቻል ስራውን መሰረት በማድረግ ከተቋቋመው ጽሕፈት ቤት ለመረዳት ተችሏል።