የለውጥ ጸር የሆኑ ሃይሎች በኦሮምያ ላይ ጦርነት መክፈታቸውን አቶ አዲሱ አረጋ ተናገሩ
( ኢሳት ዜና ሃምሌ 6 ቀን 2010 ዓ/ም ) የኦሮምያ ክልል የገጠር የፖለቲካና ድርጅት ጉዳይ ሃላፊ የሆኑት አቶ አዲሱ አረጋ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ባወጡት ጽሁፍ፣ የለውት ጸር የሆኑ ሃይሎች ኦሮሞ ከባድ መስዋትነት ከፍሎ ያስመዘገበውን ድል ለማኮላሸትና ለመቀልበስ ከምንጊዜውም በላይ እየተንቀሳቀሱ ነው ብለዋል።
እነዚህ ሃይሎች ድላችንን ዋጋ ቢስ ለማድረግና ኦሮምያን የብጥብጥ አውድማ ለማድረግ ሌት ተቀን እየሰሩ ነው ያሉት አቶ አዲሱ፣ ኦሮሞን ለማንበርከክ ከሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች አንዱ ከሶማሊ ክልል አዋሳኝ ድንበር አካባቢ ጦርነት በመክፈት ሰላማዊ ዜጎችን መግደል፣ ንብረቱን በመቀማት ማፈናቀል ይገኝበታል ብለዋል። ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ ፣ በምስራቅ ሃረርጌ ጉርሱም፣ ጭናክሰንና ባቢሌ ጦርነት ተከፍቶብናል የሚሉት አቶ አዲሱ፣ በዛሬው እለት ብቻ 3 የኦሮሞ ፖሊሶች፣ አንድ የመከላከያ አባልና 1 ሲቪል ተገድለዋል ይላሉ።
እነዚህን ያልተገባ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ጥቅም ለማግኘት በመፈለግ ጦርነት የከፈቱብንን ሃይሎች ከምንጊዜውም በላይ መዋጋት አለብን ብለዋል።
ባለፉት 2 ቀናት በቦረና ተጣቂዎችና በሶማሊ ታጣቂዎች መካከል በተካሃደው የተኩስ ለውውጥ ከ20 በላይ ሰዎች ሳይገደሉ እንዳልቀረ የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል። አብዛኞቹ የተገደሉት በሶማሊ በኩል ሲሆን፣ በቦረዎች በኩል 3 ሰዎች መሞታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል። በሶማሊ በኩል ከ 50 ያላነሱ ሰዎች መገደላቸውን የሶማሊ ክልል ለፍትህ ጥምረት የጠባለው ድርጅት ለኢሳት በላከው መግለጫ ላይ ጠቅሷል። ይሁን እንጅ ኢሳት የተገደሉትን ሰዎች ቁጥር እስካሁን በትክክል ለማወቅ አልቻለም።
የሶማሊ ክልል ለፍትህ ጥምረት መከላከያ ሰራዊት በፍጥነት ገብቶ ግጭቱን እንዲያስቆም እንዲሁም አስፈላጊው ምርመራ ተካሂዶ ወንጀለኞች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቋል።
የሶማሊ ክልል መሪ አቶ አብዲ ኢሌ ሰሞኑን የጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድን የፖለቲካ መመሪያ ደግፈው እንደሚቆሙ ተናግረው ነበር። የፌደራል መንግስት በሶማሊ በኩል የሚታየውን ግጭትና የሰብአዊ መብት ጥሰት ለማስቆም አለመቻሉ በርካታ ኢትዮጵያውያንን አስቆጥቷል። ብዙ የሶማሊ ኢትዮጵያውያን አብዲ ኢሌ ከስልጣን ቢነሳ በክልሉ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን እንዲሁም የሰብአዊ መብት ጥሰቱን ማስቆም ይቻላል በማት ይናገራሉ።
በሶማሊ ክልል በኩል እስካሁን የተሰጠ መግለጫ የለም።