በቂሊንጦ እስር ቤት የሚገኙ እስረኞች የተቃውሞ ድምጻቸውን አሰሙ
( ኢሳት ዜና ሃምሌ 6 ቀን 2010 ዓ/ም ) ከአርበኞች ግንቦት7 እና ከሌሎችም የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በተያያዘ እስረኞች ፍትህ እንዲሰጣቸው በመጠየቅ ከትናንት ሃሙስ ምሽት ጀምሮ ተቃውሞውዋቸውን እያሰሙ ነው።
እስረኞቹ፣ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ተፈተው እያለ እንዲሁም በስማቸው የተከሰሱባቸው የፖለቲካ ድርጅቶች አሸባሪዎች እንዳልሆኑ በፓርላማ ውሳኔ ተላልፎ በሚገኝበት ሰዓት እነሱ አሸባሪ ተብለው መከሰሳቸው ፍትሃዊ እንዳልሆነ ገልጸዋል። እስረኞቹ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው የተለያዩ መፍክሮችን በማሰማት ተቃውሞአቸውን ገልጸዋል።
የመንግስት ባለስልጣናት እስረኞች ላነሱት ጥያቄ ይህን ዜና እስካጠናከርንበት እኩል ቀን ድረስ መልስ አልሰጡም። በአካባቢው የተገኘ አንድ ጋዜጠኛም የእሰረኛ ቤተሰቦችን ለመጠየቅ በሄደበት ወቅት በፖሊስ ሲንገላታ የሚያሳይ ቪዲዮ ፌስ ቡክ ላይ ተለቋል።