(ኢሳት ዲሲ—ሐምሌ 3 /2018)የኢትዮጵያ ፓርላማ በአርበኞች ግንቦት 7 ፣በኦሮሞ ነጻነት ግንባር እና በኦብነግ ላይ የጣለውን ፍረጃ ማንሳቱን ሰማያዊ ፓርቲ አደነቀ።
ፓርቲው ህብረ ብሄራዊ ከሆነው ድርጅት አርበኞች ግንቦት 7 ጋር እስከ ውህደት አብሮ ለመስራት ያለውንም ፍላጎት ገልጿል።አፋኝ የሆኑት የሃገሪቱ ህጎች እንዲሻሩም ሰማያዊ ፓርቲ ጥሪውን አቅርቧል።
“ሁላችን ለአንዳችን አንዳችን ለሁላችን ስናስብ የማንወጣው። ተራራ የማንሻገረው ገደል አይኖርም ! “ በሚል ርዕስ ሰማያዊ ፓርቲ ዛሬ ሃምሌ 3/2010 ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያውያኑ ድርጅቶች ላይ የተጣለው ፍረጃ በፓርላማ መነሳቱን በማድነቅ እና በማበረታት አስስቀድሞም ቢሆን መደረግ ያልነበረበት ርምጃ ነው ሲል ገልጾታል።
በፍረጃው ሳቢያ በዜጎች ላይ ለደረሰው ሰቆቃ የታሪክ ተጠያቂዎች መኖራቸውንም አመልክቷል።አርበኞች ግንቦት 7 ፣ኦነግም ሆነ ኦብነግ አሸባሪዎች ሳይሆኑ የመብት ተሟጋቾች ናቸው ሲል ምስክርነት የሰጠው ሰማያዊ ፓርቲ ህብረ ብሄራዊ ከሆነው ድርጅት አርበኞች ግንቦት 7 ጋር እስከ ውህደት አብሮ ለመስራት ያለውንም ፍላጎት ገልጿል።አፋኝ የሆኑት የሃገሪቱ ህጎች እንዲሻሩም ሰማያዊ ፓርቲ ጥሪውን አቅርቧል።ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በጎ ርምጃዎች ምስጋነውን በማቅረብም ጥያቄውን አስከትሏል፦
“ በጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አህመድ የሚመራው መንግስት ይሄንን አሳዛኝ የታሪካችን ምዕራፍ ለመዝጋት እና የሃሳብ ብዝሃነትን የምታስተናግድ አገር እውን ለማድረግ በተለያዩ የፖለቲካ መስመር ተደራጅተው ሲታገሉ ለነበሩትን የፖለቲካ ተዋናዮች ጥሪ ማቅረባቸው የምንደግፈው ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡ ሆኖም እነዚህን ድርጅቶች ሆነ በተለያየ አካባቢ መብቶቻቸውን ለማስከበር ትጥቅ አንግበው በዱር በገደሉ የሚዋደቁት ዜጎቻችን፤ ለዚህ ያበቃቸው መሰረታዊ የሰብዓዊና የዲሞክራሲ ጥያቄ እውን ለማድረግ የሰው ሃይል፣ ትጥቅና ስንቅ አደራጅተው እየተንቀሳቀሱ የነበረ፤ እንደ ዜጋ ለዲሞክራሲ መስፈን መስዋዕት ለመሆን የተዘጋጁና ከቤት ንብረታቸው ተለይተው የነበሩ መሆናቸውን ሰማያዊ ፓርቲ ይገነዘባል፡፡ “
በማለት የቀጠለው መግለጫ
“ እነዚህ ድርጅቶችም ሆነ ሌሎች ቀድመው በሰላማዊ መንገድ ሲታገሉ የቆዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴያቸውን አፍኖ የነበረው የተለያዩ ህገ መንግስቱ ድንጋጌዎች፤ የሲቪክ መብት ፣የመደራጀትና የሰብአዊ መብት መከበርን የሚጻረሩ አዋጆች እንዲሁም ተቋማት ነጻ፣ ገለልተኛ እና ፍትሃዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ የሚያስችል እርምጃ በቀጣይ በተጨባጭ ማከናወን ካልተቻለ ለዲሞክራሲ ትግሉ ” እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው” እንዳይሆን ትልቅ ስጋት እዳለው ሰማያዊ ፓርቲ ሳይገልጽ አያልፍም፡፡ “ ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል።
ሰማያዊ ፓርቲ ከኤርትራ ጋር የተጀመረውን የሰላም ጥረትም በመግለጫው አድንቋል።