(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 2/2010)በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች የድጋፍ ሰልፎች ተካሄዱ።
አርባምንጭ ከ1ሺህ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ለእይታ የበቃበት ደማቅ ሰልፍ መካሄዱ ታውቋል።
በእንጅባራ፣ ዳንግላ፣ ዳባት፣ አብርሃጅራና ሶረቃ ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር የተመዘገበባቸው የድጋፍ ሰልፎች መደረጋቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በራያ ወሎና በሰሜን ሸዋ አጣዬ በተደረጉት ሰልፎች ታጣቂዎች ህዝቡ ላይ መተኮሳቸው ታውቋ። የሰው ህይወት መጥፋቱንም ለማወቅ ተችሏል።
በየከተሞቹ በተደረጉት ሰልፎች ህወሃትን የሚያወግዙ መልዕክቶች ተላልፈዋል።
በራያ ዋጃና ጥሙጋ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የተካሄደውን ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ተከትሎ የተፈጠረው ግጭት እስከዛሬ ድርስ በአከባቢው ውጥረት ማንገሱን ነው ከስፍራው የደረሰን መረጃ የሚያመለክተው።
የራያ ህዝብ የማንነት ጥያቄውን በማንሳቱ ምክንያት የአከባቢው ባለስልጣናት የታጠቁ ሃይሎችን መላካቸው የተገለጸ ሲሆን ከህዝብ በደረሰባቸው ተቃውሞ የተኩስ እሩምታ መክፈታቸው ታውቋል።
በአስለቃሽ ጢስ የተጀመረው ግጭት ጥይት በመተኮስ የቀጠለ ሲሆን በርካታ ሰዎች መጎዳታቸውን ለማወቅ ተችሏል።
በትላንትናው ዕለት የነበረው ውጥረት ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት የመረጃ ምንጮች የራያ ማንነት ጥያቄ ኢ ህገመንግስታዊ ነው በሚል በአከባቢው የህወሀት ባላስልጣናት ጥቃት እንደደተፈጸመ አስታውቀዋል።
በሰሜን ሸዋ አጣዬም የሰው ህይወት የጠፋበት ግጭት መፈጠሩ ታውቋል። የመሳሪ ግምጃ ቤት መዘረፉ የተገለጸ ሲሆን በግጭቱ ታጣቂዎቹን ጨምሮ አምስት ሰዎች መገደላቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በአማራ ክልል በእንጅባራ ዳንግላ ዳባት አብረሃጅራና ሶረቃ የተካሄዱት ሰልፎች ከፍተኛ የህዝብ ቁጥር የታየባቸውና በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ያሸበረቁ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።
በእንጅባራ ረጅም የተባለ ሰንደቅ ዓለማ በከተዋማ ዋና መንገድ ላይ ለዕይታ የቀረበ ሲሆን የተለያዩ መልዕክቶች ተስተጋብተዋል።
በተለይም የህወሀትን ቡድን የሚያወግዙና የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን የለውጥ ጅምር የሚያወድሱ መልዕክቶች መሰማታቸውን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
በዳንግላም ተመሳሳይ ትዕይንተ ህዝብ የተካሄደ ሲሆን የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ትዕይንቱ አድምቆት እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።
በአህብራሃ ጅራና ሶሮቃም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን በመደገፍ ደማቅ ትዕይንተ ህዝብ መካሄዱ ታውቋል።
ለቅዳሜ ተጠርቶ የነበረው የአርባምንጩ የድጋፍ ሰልፍ በከተማው አስተዳደር አንዳንድ አመራሮች ምክንያት ለዛሬ ተላልፎ ነበር።
ዛሬ አርባምንጭ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አሸብርቃ ነው የዋለችው። የደቡብ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ኮከቦች ህብረት ባስተባበረው በዚሁ ሰልፍ 1ሺህ600 ሜትር ርዝመት ያለው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ መታየቱን ለማወቅ ተችሏል።
በግፍ ለህወሃት ካድሬዎች የተሸለመው የአርባ ምንጭ እርሻ ልማት በአስቸኳይ ለአካባቢው ወጣቶች እንዲሰጥ፡ በግፍ ለህወሃት ካድሬዎች የተሸለመው የሲሌ እርሻ ልማት በአስቸኩይ ለአካባቢው ወጣቶች እንዲሰጥ ፡ ህወሓትና የትግራይ ህዝብ የተለያዩ ናቸው፡ ያልታደሱና የአሮገው ዘመን ቁማርተኞች የደኢህዴን ባለስላጣናት ስልጣን ልቀቁ የሚሉ መፈክሮች መሰማታቸውን ከአከባቢው ከደረሰን መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በካና ቶሮንቶ ኢትዮጵያውያን ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ድጋፋቸውን ለማሳየት በትላንትናው ዕለት ሰልፍ ማደረጋቸው ታውቋል።
በሰልፉ ላይ ኤርትራውያን በመገኘት አጋርነታቸውን ማሳየታቸውን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።