(ኢሳት ዲሲ–ሐምሌ 2/2010) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በኤርትራ ለሁለት ቀናት ባደረጉት ጉብኝት የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደገና መጀመሩን ጨምሮ በወደብ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ዘርፎች ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ ጋር ስምምነት ተፈራረሙ።
የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ በጉዳዩ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር ለመነጋገር ዛሬ አዲስ አበባ ገብተዋል።
ከ20 አመታት በኋላ ሁለቱ ሃገራት በመሪዎች ደረጃ ያደረጉት ግንኙነትና የነበረው ደማቅ አቀባበል የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ስቧል።
እሁድ ሐምሌ 1 ቀን 2010 ማለዳ አስመራ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ አቀባበል የተደረገላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአስመራ ጎዳናዎች እጅግ ደማቅ አቀባበል ጠብቋቸዋል።
ከአውሮፕላን ማረፊያው እስከ አስመራ ቤተመንግስት የነበረውን እጅግ ደማቅ አቀባበል ኢትዮጵያውያንን ያስደነቀ መሆኑን መረዳት ተችሏል።
የሕዝቡን የሰላም ፍላጎትና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያለውን ወንድምነት ያሳየበት ትዕይንት ሲሉም አንዳንዶች ገልጸውታል።
ሁለቱ መሪዎች በቤተመንግስት የእራት ግብዣ ላይ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እጅግ ወሳኝ የሚባሉ ስምምነት ማድረጋቸውም ተመልክቷል።
የዲፕሎማሲ ግንኙነታቸውን እንደገና ለመጀመር ሁለቱ ሃገራት ኤምባሲዎቻቸውን በአዲስ አበባና አስመራ ለመክፈት ተስማምተዋል።
የሁለቱ ሃገራት አየር መንገዶችም ወደ ሁለቱ ሃገራት እንዲበሩ ስምምነት ላይ ተደርሷል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደሌሎች ሃገራት በሚያደርገው በረራም በኤርትራ የአየር ክልል እንዳያልፍ የተደረገበት እገዳም በስምምነቱ መሰረት ተነስቷል።
ከ20 አመታት በላይ በሁለቱ ሃገራት መካከል የተቋረጠው የስልክ ግንኙነትም ከትላንት ጀምሮ በይፋ ቀጥሏል።
በወደብ አጠቃቀም ላይም ከስምምነት መድረሳቸው ተመልክቷል።
ለክብራቸው በአስመራ ቤተመንግስት በተካሄደው የእራት ግብዣ ላይ በአማርኛና በትግርኛ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በሁለቱ መሪዎች መካከል የተደረገውን ስምምነት ይፋ አድርገዋል።
በነበረው አቀባበል በጣም በመደሰታቸው ሃሳባቸውን በአማርኛም ይሁን በትግርኛ ለመግለጽ መቸገራቸውን ገልጸዋል።
በጦርነቱ ለሞቱትና ለተጎዱት ሃዘናቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወንድማማችነቱን የማጠናከሩ ስራ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በአስመራና በአዲስ አበባ እንደልባቸው መንቀሳቀስ የሚችሉበት መሰረት መጣሉንም አስረድተዋል።
ከትግራይና አፋር ሕዝብ ጋር በተያያዘ አንዳንድ አክቲቪስቶችና የሚታወቁ የፖለቲካ ሰዎች የሚናገሩትን አትስሙ፣ እነሱም ለእናንተ ፍቅር አላቸው።እናንተም ለእኛ ያሳያችሁትን ፍቅር አትንፈጓቸው ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም ባደረጉት አጭር ንግግር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የወሰዱት ርምጃ ቀላል እንዳልሆነም አመልክተዋል።
ከእንግዲህ የሚገጥመንን ችግርም ሆነ እድል አብረን እንወጣዋለን ያሉት ኢሳያስ አፈወርቂ የኤርትራና የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
በኢትዮጵያና በኤርትራ መሪዎች መካከል የተደረገውን ግንኙነት የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ፖል ካጋሚም አወድሰውታል።
የሩዋንዳ ፕሬዝዳንትና የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ፖል ካጋሚ ለተግባራዊነቱም ከሁለቱ መንግስታት ጎን እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል።
የዛሬ 20 አመት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ጦርነት ሲፈነዳ ለሽምግልና ከተንቀሳቀሱ ቀዳሚ ሃገራት አንዷ ሩዋንዳ ነበረች።
ሩዋንዳ የሽምግልና ጥረቱን የጀመረችው ከአሜሪካ ጋር ነበር።
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ታሪካዊ የአስመራ ጉዞና ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ ጋር የተደረገውን ስምምነት ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሃፊ ዛሬ አዲስ አበባ ገብተዋል።
ሚስተር አንቶኒዮ ጉተሬዝ አዲስ አበባ የገቡት በኢትዮጵያና በኤርትራ መሪዎች መካከል የተደረገውን ስምምነት በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር ለመወያየት እንደሆነም ተመልክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም የሁለት ቀናቱን የኤርትራ ጉብኝት አጠናቀው አዲስ አበባ ገብተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የኤርትራ ጉዞና ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቄ ጋር ያደረጉትን ስምምነት የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንንም ትኩረት ስቧል።
“በጠላትነት የተማማሉት ኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነቱ ማብቃቱን አወጁ” በማለት የአሜሪካው ሲ ኤን ኤን ሲዘግብ “ኢትዮጵያና ኤርትራ የሰላምና የወንድማማችነት ስምምነት ፈረሙ”ያለው ደግሞ ዋና መቀመጫውን በዶሃ ኳታር ያደረገው አልጀዚራ ነው።
ቢቢሲም ኢትዮጵያና ኤርትራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እንደገና ጀመሩ፣የጦርነቱንም ማብቃት አወጁ ብሏል።
ዋሽንግተን ፖስት የኢትዮጵያው መሪ ከ20 አመት በኋላ ወደ ኤርትራ ታሪካዊ ጉዞ አደረጉ ሲል በዘገባው አስፍሯል።
የፈረንሳዩ ፍራንስ 24 ደግሞ “ኢትዮጵያና ኤርትራ ከታሪካዊው የሁለቱ መሪዎች ውይይት በኋላ የቀድሞ ግንኙነታቸውን መለሱ ሲል ዘግቧል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል ደግሞ “ በመራራ ጥላቻ ውስጥ ያሉት ኢትዮጵያ ኤርትራ ታሪካዊ ንግግር ጀመሩ”ብሏል።
ሌሎች በርካታ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንም በተለያዩ ቋንቋዎች ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ዘግበውታል።