ኦነግ፣ ኦብነግና ግንቦት 7ን በሽብርተኝነት የፈረጀው ፓርላማ ፍረጃውን አነሳ
(ኢሳት ዜና ሰኔ 28 ቀን 2010 ዓ/ም) ሟቹ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት በፓርላማው በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ ያስደረጓቸው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ድርጅቶች የሆኑት፣ የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር፣ የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጭ ግንባርና አርበኞች ግንቦት7፣ ዛሬ በዚያው ፓርላማ ፍረጃው እንዲነሳላቸው ተደርጓል።
ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ቃል በገቡት መሰረት የተላለፈው ይህ ውሳኔ ፣ የሃይል አማራጭን ተጠቅመው ትግል ሲያደርጉ የነበሩትን ድርጅቶችን ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንዲገቡ ያደጋቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።
የቀድሞ የኦነግ አባላት የሆኑት እና የአሁኖቹ የአዴግ አመራሮች እነ አቶ ሌንጮ ለታ ቀደም ብለው ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል። ሌላው የኦነግ አመራር የነበሩት ብ/ጄ ከማል ገልቹም እንዲሁ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል። በዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግም የዶ/ር አብይን የሰላም ጥሪ እንደሚቀበል አስታውቋል።
በኦጋዴን ነጻ አውጭ በኩል ግን እስካሁን የተሰጠ መግለጫ የለም።
አርበኞች ግንቦት7 የጠ/ሚኒስትሩን ጥሪ በአዎንታ እንደተቀበለውና የኢትዮጵያ ህዝብም የለውጡን እንቅስቃሴ እንዲደግፍ ጥሪ አቅርቧል።