የጸረ ሽብር ሕጉንና ሌሎች ሕጎችን አጥንቶ የሚያሻሽል ቡድን ተቋቋመ

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 27/2010)የጸረ ሽብር ሕጉን እንዲሁም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የመገናኛ ብዙሃን ሕግን አጥንቶ የሚያሻሽል የባለሙያዎች ቡድን ተቋቋመ።

ታዋቂ የሕግ ባለሙያዎችና የዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰሮች የሚገኙበት ይህ ቡድን ሕጎቹን ከሃገሪቱ ሕገ መንግስት ፣ከሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ጋር በተጣጣመ መንገድ እንዲያሻሽል ሃላፊነት እንደተሰጠውም መረዳት ተችሏል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ መምህር ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ፣የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር መስራችና ፕሬዝዳንት የነበሩት ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ፣ታዋቂው የሕግ ጠበቃ አቶ ታምሩ ወንድማገኘሁን ጨምሮ ከፍተኛ የሕግ እውቀትና ልምድ ያላቸው ባለሙያዎች የተካተቱበት ይህ ቡድን የተጠቀሱን ሕጎች በመመርመር ሙያዊ ድጋፍ ከመስጠት ባሻገር በሌሎች ሕጋዊ ጉዳዮች ላይም መንግስትን ያማክራል ተብሏል።

የሕግ ባለሙያዎቹ አማካሪ ቦርድ ቋሚ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት እንደሚኖረውም ተገልጿል።

ፕሮፌሰር ጥላሁን ተሾመ፣ ፕሮፌሰር ዘካርያስ ቀንአ፣አቶ ታምሩ ወንድማገኘሁ፣ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ፣አቶ ሰለሞን አረዳ፣አቶ ማሞ ምህረቱ፣ዶክተር በላቸው ወርቁ፣አቶ ሊቁ ወርቁ፣አቶ ታደለ ነጋሽ፣ወይዘሮ መሰረት ስዩም፣ወይዘሮ ሰምሃል ጌታቸው፣አቶ አሊ መሃመድ፣ዶክተር ዘውድነህ በየነን ጨምሮ ታዋቂ የህግ ባለሙያዎችና ምሁራን የተካተቱበት የፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ቦርድ አወዛጋቢ የሆኑ ሕጎችን ጨምሮ በሌሎች የሕግ ጉዳዮች ላይም ምርመራ በማድረግ ለመንግስት የማማከር ስራ እንደሚሰራም ለማወቅ ተችሏል።