የድጋፍ ሰልፉ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 25/2010) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የጀመሯቸውን የለውጥ ርምጃዎች የሚደግፉ ሰላማዊ ሰልፎች በተለያዩ ክልሎችና ከተሞች እንዲሁም ከኢትዮጵያ ውጭም ባሉ ኢትዮጵያውያን ዘንድ መቀጠላቸው ታወቀ።

በተለይም በባህርዳር ከተማ የተካሄደው እጅግ ደማቅ ትዕይንተ ሕዝብ የብዙዎችን ትኩረት የሳበ መሆኑም ታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድም ሕዝቡ ለሰጣቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ከመቶ ሺህ ሕዝብ በላይ የታደመበት የባህርዳሩ ትዕይንተ ሕዝብ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ሰብአዊ መብት የሚረገጥበት ሁኔታ እንደማይደገምና መንግስትና ሕዝብ የሚደማመጥበት ሁኔታ እንደሚከተል ቃል ገብተዋል።

የክልሉ ፕሬዝዳትን አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው ከእንግዲህ አማሮች የሚሰደዱበት፣የሚሸማቀቁበት ሁኔታ እንደማይኖር ቃል ገብተዋል።

ከቁዘማም የሚላቀቁበት ጊዜም እንደሆነም በአጽንኦት ተናግረዋል።

ከአካባቢያዊና ክልላዊ ስሜት በመውጣት በሃገራዊ ስሜት ለኢትዮጵያ አንድነት መስራት እንደሚገባም አሳሰበዋል።

ለውጡን ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችንና ቡድኖችን የአሮጌው ዘመን ቁማርተኞች ሲሉ ገልጸዋቸዋል።

ይህ ጥረታቸው አይሳካላችውም ብለዋል።

“አንድ መሆናችን እንቅልፍ የነሳቸው ያልታደሰው የአሮጌው ዘመን ቁማርተኞች እግራችንን እየተከተሉ ሰላማችንን ለማወክ እየጣሩ ነው።ግን አልተሳካላቸውም ነው ያሉት”

በዚህ መድረክ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ የለውጥ ሒደቱን ለመቀልበስ የሚደረገው ሙከራ ተቀባይነት እንደሌለው አሳስበዋል።

የለውጡን ሒደት በመደገፍ መሰለፋቸውንም አስታውቀዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የተካሄዱ አፈናዎችና ጭቆናዎችን በማውገዝ የለውጥ እንቅስቃሴ በማድረግ ከ10 አመታት በላይ በወህኒ የቆዩት ወይዘሮ እማዋይሽ አለሙ በእለቱ የክብር እንግዳ ነበሩ።

ወይዘሮ እማዋይሽ አለሙ የተጀመረው እንቅስቃሴ ወደ ሽግግር መንግስት ይወስደናል ወይንስ እናንተ በቀደዳችሁት ቦይ እንድንፈስ ነው የምትፈልጉት የሚል ጠንካራ ጥያቄ አንስተዋል።