(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 22/2010) ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው በሀገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎች ካሉባቸው ሀገራት አንዷ ሆናለች ሲል የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ገለጸ።
ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ለማስከበር ህዝብ ተስፋ የጣለበት አጋጣሚ እንዳይባክን በሚል ርዕስ ሰመጉ ባወጣው መግለጫ በሚሊየን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የዚህ ክልል ተወላጆች አይደላችሁም በሚል ከሚኖሩባቸው አከባቢዎች እየተፈናቀሉ ናቸው ብሏል።
እነዚህ በሐገር ውስጥ የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ ይገኛሉም ሲል ሰመጉ በመግለጫው አስታውቋል።
አሁን የሚታየው መልካም ጅምር እንዳይቀለበስ ሁሉም የሚመለከተው አካል ሃላፊነቱን እንዲወጣ የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ጥሪ አድርጓል።
የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ሰመጉ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መልካም ጅምሮች አድናቆቱን በመግለጽ ይህን ተስፋ የሚቀለብሱ ድርጊቶች እየተፈጸሙ ነው በማለት ስጋቱን የገለጸበትን መግለጫ ነው ዛሬ ያወጣው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ስልጣን ከያዙ ወዲህ የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች የሰቆቃው ዘመን ወደ ማብቂያ ለመቃረቡ አመላካቾች እንደሆኑ ሰመጉ በጽኑ ያምናል ይላል መግለጫው።
በውጭ ሀገራት ለሚገኙ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሃይሎች ጥሪ ማቅረባቸው ለብሄራዊ ዕርቅ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍትም ነው ብሏል።
ይሁንና ይህን ተስፋ ሰጪ ጅምር ሊያደበዝዙ ወይም ሊቀለብሱ የሚችሉ ሁኔታዎች መታየታቸው ድርጅታችንን በእጁጉ ያሳስበዋል ሲል የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ስጋቱን ገልጿል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ኑሮአቸውን መስርተው ለዓመታት ከኖሩበት ቀዬ የዚህ ክልል ተወላጆች አይደላችሁም በሚል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለዘመናት ከኖሩባቸው አከባቢዎች መፈናቀላቸው ተጠናክሮ ቀጥሏል።
ሰመጉ አያይዞም በእነዚህ ተፈናቃዮች በጊዜያዊነት በተጠለሉባቸው አከባቢዎች ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ ተከስቷል ሲል የአደጋውን አሳሳቢነት በመግለጽ ጠቅሷል።
የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች መስሪያ ቤት ኦቻ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት በጉጂና ጌዲኦ መሀል በተነሳው ግጭት የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ወደ 1ሚሊየን መድረሱን ገልጿል።
በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች መሀል በተነሳው ግጭትም 1ነጥብ 2 ሚሊየን የሚሆን ህዝብ መፈናቀሉን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በተመሳሳይ ግጭቶች የተፈናቀሉትን ሲጨምር ከ2ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያዊ በሀገር ውስጥ መፈናቀሉን ለመረዳት ተችሏል።
የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ዛሬ ባወጣው መግለጫው በሀገር ውስጥ መፈናቀል ከፍተኛ ቁጥር በመያዝ ከሚጠቀሱ የዓለም ሀገራት ኢትዮጵያ አንዱ መሆኗን ገልጿል።
ድርጅቱ በቤንሻንጉል ጉምዝ፡ በጉጂና ጌዲኦ በቄሌም ወለጋ የተፈናቀሉትን ኢትዮጵያውያን በተመለከተ ከቦታዎቹ ያሰባብሰባቸውን በመጥቀስ የመፈናቀሉ አደጋ አዝማሚያው ያሳስባል ብሏል።
በመሆኑም መንግስት አፋጣኝ እርምጃ በመወሰድ የዜጎችን ስቃይና መከራ እንዲያበቃ ያደርግ ዘንድ የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ሰመጉ ጥሪ አድርጓል።
የህግ ተቋማት ገለልተኛ ሆነው በአዲስ መልክ እንዲደራጁ፣ በእስር ላይ የሚገኙ ቀሪ ሰዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፣ አፋኝ አዋጆችና ህጎች ማሻሻያ እንዲደረግላቸው፣ ነጻና ገለልተኛ መገናኛ ብዙሃን እንዲፈጠሩና ያሉትም ከአፈና እንዲላቀቁ፣ በሁለቱም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ወቅት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ አካል እንዲጣሩና ይህን የፈጸሙ የመንግስት አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡ የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ በመግለጫው ጠይቋል።