በእስር ቤት ውስጥ በሚፈፀምባቸው ድብደባ ለሕይወታቸው እንደሚሰጉ ተከሳሾች ለፍርድ ቤቱ ገለፁ
(ኢሳት ዜና ሰኔ 22 ቀን 2010 ዓ/ም)ከቂሊንጦ እስር ቤት ቃጠሎ ጋር በተያያዘ በእነ አርጋው ሞገስ የክሰ መዝገብ የተከሰሱት አርጋው ሞገስና ቴዎድሮስ ዳንኤል ፍርድ ቤት ቀርበው እውነታውን በመናገራቸው ብቻ በቂሊንጦ እስር ቤት ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመባቸው ለፍርድ ቤቱ ገለጹ። ተከሳሾቹ ዛሬ ሰኔ 22 ቀን 2010 ዓ.ም በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 3 ወንጀል ችሎት ቀርበው በድብደባ የተጎዳውን አካላቸውን ለፍርድ ቤቱ አሳይተዋል።
1ኛ ተከሳሽ አቶ አርጋው ሞገስ ግራ እጁ በፋሻ ተጠቅልሎ ከአንገቱ ጋር ታስሮ የመጣ ሲሆን አራት የእጅ ጣቶቹ መሰበራቸውን ለፍርድ ቤት ተናግሯል። እንዲሁም እግሩ ላይ በሚስማር መመታቱንም ለችሎቱ አሳይቷል። አራቱ የእጅ ጣቶቹ መጎዳታቸውን የሚያሳይ የህክምና የራጅ ውጤትም ለፍርድ ቤቱ አሳይቷል። በተመሳሳይ የቀኝ እጁ በፋሻ የታሸገው አቶ ቴዎድሮስ ዳንኤልም ፍርድ ቤት መጥቶ በሚናገረው እስር ቤት ውስጥ ድብደባ እንደተፈፀመበት ገልፆአል። ልብሱን አውልቆ በድብደባ የበለዘ ሰውነቱን ለፍርድ ቤቱ አሳይቷል።
ተከሳሾቹ እስር ቤት ውስጥ አብራራው በሚባል ግለሰብ ትዕዛዝ መደብደባቸውም ገልፀዋል። ድብደባ የተፈፀመባቸው ጭንብል ባጠለቁ ሰዎች አማካኝነት እንደሆነ በመግለፅ “በእስር ቤቱ
ውስጥ የተደራጀ የማፍያ ቡድን አለ” በማለት ገልጸዋል።
ተከሳሾቹ “እስር ቤት ውስጥ የተደራጀ ቡድን አለ፣ እስር ቤት ውስጥ ያለው አይ ኤስ ነው፣ ውጭ ያለው ሕዝብ እንደመር እያለ እኛን እየቀነሱን ነው። ከቂሊንጦ እስር ቤት ካላስወጣችሁን በሚቀጥለው የሚመጣው አስከሬናችን ነው። ከፈለጋችሁ ወደ ሌላ እስር ቤት ላኩን” ሲሉ በቂሊንጦ እስር ቤት በሚፈፀምበቸው ድብደባ ለሕይወታቸው እንደሚሰጉ መናገራቸውን ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው በፌስቡክ ገጹ ላይ ዘግቧል።