ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በአፋር ክልል ከህዝቡ ጋር ተወያዩ። የተወሰኑ የአፋር ምሁራንና ወጣቶች ተነጥለው በውይይቱ እንዳይገኙ ከመደረጋቸውም ባሻገር ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ታወቋል።
(ኢሳት ዜና ሰኔ 21 ቀን 2010 ዓ/ም) ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ከክልሉ ነዋሪዎች ጋር ሕዝባዊ ውይይት አደርገዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩን መምጣት ተከትሎ የክልሉ ገዢ ፓርቲ የሆነው የአፋር ሕዝብ ዴሞክራሲያ ፓርቲ (አ.ብ.ዴ.ፓ.) የፓርቲውን አባላትና ደጋፊዎችን ከተለያዩ ከተሞች በማምጣት አስተዳደራዊ ቅሬታዎች እንዳይሰሙ አድርጓል።
በክልሉ የተንሰራፋውን ሌብነት፣ የዘመድ አዝማድ አሰራር፣ ኋላቀርነትና የህወሃትን ጣልቃ ገብነት ያጋልጣሉ የተባሉ ግለሰቦች ላይም አካላዊ ጉዳቶች ተፈጽሞባቸዋል። ቁጥራቸው ከሰማኒያ በላይ የሚሆኑ ወጣቶችና የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንም ካለ ፍትሕ ታስረዋል። ወጣቶችን በመደገፍ የምትታወቀውና የከተማው ፖሊስ ሰራዊት አባል የሆነችው ሳዲያ አህመድ በድብደባ ጉዳት ከደረሰባቸው ውስጥ አንድዋ መሆኗን የአፋር ሰብዓዊ መብት ታጋይ ወጣት አካድር ኢብራሂም ገልጸዋል።
የአፋር ክልል፣በኢትዮጵያ ኋላቀር ክልል ተብለው ከማእከላዊ መንግስት ተጨማሪ በጀት ከሚመደብላቸው ክልሎች አንዱ ቢሆንም፣ የክልሉ ነዋሪዎች አሁንም የልማቱ ተጠቃሚዎች መሆን አልቻሉም።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ዛሬ ለተገኙት ተሰብሳቢዎች ባሰሙት ንግግር “የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ላይ የሚፈጠሩ ዘርፈ-ብዙ ችግሮችን ለመፍታት በአንድነት ከጎናችን ሆናችሁ ጥንካሬ እንደምትጨሩረልን አንጠራጠርም። ምክንያቱም አንድም ቀን ለኢትዮጵያ ፍቅርን ለባንዲራ ፍቅርን አሳንሳችሁ አታውቁምና!” በማለት የአፋር ህዝብ ለኢትዮጵያዊነት ምስረታ ላበረከቱት አስተዋጾ አመስግነዋል። ወደፊትም የተለመደው አጋርነታቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።