በአማራ ክልል በግጭት ለሞቱና ለቆሰሉ ወገኖች ካሳ ሊከፈል ነው

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 21/2010) በአማራ ክልል ላለፉት አመታት በተካሄደው ግጭት ለሞቱና ለቆሰሉ ወገኖች የክልሉ መንግስት ካሳ ለመክፈል መወሰኑን አስታወቀ።

የአማራ ክልል የመንግስት ኮሚኒኬሽን ክፍል ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ የክልሉ መንግስት ለሰለባዎቹ አጋርነቱን ለመግለጽ ያህል የካሳ ክፍያ እንደሚፈጽም አረጋግጠዋል።

በዚህም መሰረት ሰለባ ለሆኑ ወገኖች ቤተሰቦች ለእያንዳንዳቸው 75 ሺ ብር እንደሚከፈል ተገልጿል።

አካላቸው ጎሎ መስራት ለማይችሉ ወገኖች ደግሞ 50 ሺ ብር ካሳ እንደሚከፈል ተገልጿል።

ለሌሎች ቁስለኞች 25 ሺ ብር እንደሚከፈልም ተመልክቷል።

በአማራ ክልል የተነሳውን ሕዝባዊ ጥያቄ ተከትሎ የመንግስት ሃይሎች በወሰዱት ርምጃ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል።