(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 21/2010)በአሶሳ ከተማ ከማክሰኞ ጀምሮ የተፈጠረው ግጭት በገንዘብ በተገዙ ግለሰቦች የተፈጸመ መሆኑን የክልሉ ፕሬዝዳንት አስታወቁ።
ገንዘቡን የከፈሏቸውና ለዚህ ድርጊት ያሰማሯቸው እነማን ናቸው የሚለው በምርመራ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።
በግጭቱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 9 የደረሰ ሲሆን በግጭቱ የቆሰሉ ሰዎች ቁጥርም 49 መድረሱ ይፋ ሆኗል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በአማራ ክልል በባቲና በአንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረ ግጭት በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።
በባቲም ግጭቱን የቀሰቁት ሰዎች በአካባቢው የማይታወቁ መሆናቸውን ሰለባዎቹ ተናግረዋል።
ከክልሉ መንግስት አቅም በላይ የሆነውና በአሶሳ ከተማ የተፈጠረው ግጭት በመከላከያ ሰራዊት ጣልቃ ገብነት ከትላንት ጀምሮ ጋብ ማለቱ ታውቋል።
አሶሳ ከተማ ሙሉ በሙሉ በመከላከያ ሰራዊቱ ቁጥጥር ስር መሆኑም ተመልክቷል።
ለ9 ሰዎች ሞትና ለ49 ሰዎች አካል መጉደል ምክንያት ናቸው የተባሉና በግጭቱ መቀስቀስ የተጠረጠሩ ግለሰቦችም በቁጥጥር ስር በመዋል ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል።
የቤንሻንጉል ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ አሸድሊ ሃሰን ለመንግስት መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ግጭቱን የቀሰቀሱት በገንዘብ የተገዙ ግለሰቦች ናቸው ብለዋል።
እነዚህን ግለሰቦች ያሰማራቸውና ገንዘብ የሰጣቸው አካል ማነው በሚለው ጉዳይ ላይ ምርመራ መጀምሩንም አስታውቀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በአማራ ክልል በባቲና በአንዳንድ አካባቢዎች ግጭት መፈጠሩን የሚያመለክቱ መረጃዎች ወተዋል።
በተፈጠረው ግጭትም በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል።
እንደ መረጃዎቹ ከሆነ በአካባቢዎቹ ግጭቱን የቀሰቁት ሰዎች በነዋሪው ዘንድ የማይታወቁ መሆናቸውን ሰለባዎቹ ተናግረዋል።