በኢትዮጵያ የተጀመሩ ለውጦችን ለማደናቀፍ የሴራ ፖለቲካ እየተካሄደ ነው ተባለ

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 21/2010) በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የለውጥ ሂደት ለማደናቀፍ የቴሌኮም ኔትዎርክን ከመጥፋት ጀምሮ የተደራጁ ሥራዎች በመሰራት ላይ መሆናቸውን መንግስት አስታወቀ።

ይህንን የማደናቀፍ ሴራ የሚመረምሩ ኮሚቴዎች መዋቀራቸውም ተመልክቷል።

አጥፊዎቹን ለፍርድ ለማቅረብ በሚደረገው ሂደት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመንግስት ጎን በመቆም አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ጠይቋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት እንዳስታወቀው ሰኔ 16/2010 በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የተካሄደውን ሰላማዊ ሰልፉን ለማደናቀፍ ቦምብ ከመወርወር ጀምሮ ሂደቱ እንዲስተጓጎል በወቅቱ የመብራትና የቴሌኮም ኔትወርክ የማጥፋት ሥራ ተከናውኗል።

ከዚህም በተጨማሪ የኢኮኖሚ አሻጥርም በተደራጀ አኳኋን በመስራት የኑሮ ውድነት እንዲባባስ እና የተለያዩ ህዝባዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስፈላጊውን አገልግሎት እንዳይሰጡ እየተደረገ መሆኑንም መንግስት ይፋ አድርጓል ።

ይህንን በተደራጀ መንገድ እየተካሄደ ያለውን እና የለውጥ ሂደቱን ለማደናቀፍ የሚፈጸመውን ሴራ የሚመረምር እና ወንጀለኞቹንም ለፍርድ የሚያቀርቡ ኮሚቴዎች መዋቀራቸውም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ሕዝብም ሂደቱን ለማገዝ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግም ጥሪ ቀርቧል።

የምርመራው ሂደት እና ውጤቱም ለሕዝብ ይገለጻል ተብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በሃገሪቱ የተፈጠረውን መረጋጋት የሚያውኩ ግጭቶች በአሁኑ ሰዓት በማገርሸት ላይ ይገኛሉ።

ይህ እየተካሄደ ያለውን ግጭት በለውጥ ሂደቱ የተገፋው ቡድን እያቀነባበረው እና እየመራው መሆኑ በተለያዩ ወገኖች ቢገለጽም ፣የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ግጭቶቹን በተመለከተ በመግለጫው  አልጠቀሰም።