(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 19/2010) የጎንደር ሕዝብ የወልቃይት ጉዳይን የማንሳት መብት እንደሌለው የሕወሃቱ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረ ሚካኤል ገለጹ።
የወልቃይት ነዋሪዎች ጎንደሮችን የሚያስታግስልን መንግስት አጣን እያሉን ነው ሲሉ ዶክተር ደብረጺዮን አማረዋል።
ድንበራችን ተከዜ ነው የሚሉት ጎንደሮች ሀሳባቸው ኋላቀር ቢሆንም ሕገመንግስቱ ግን ሌላ ነው ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ኬርያ ኢብራሂም ስለወልቃይት የጻፉት ደብዳቤም የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴን በእጅጉ አስቆጥቷል።
የወልቃይት ጉዳይን በተመለከተ በውክልና ወይንም በደብዳቤ የሚጠየቅ ሳይሆን በሕገመንግስት የተቀመጠና ጉዳዩ የተቋጨ መሆኑን የህወሃቱ ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጺዮን ተናግረዋል።
የወልቃይት የማንነት ኮሚቴ አባላትም ሕዝብ የወከላቸው አይደሉም ብለዋል።
በጎንደር የወልቃይትን ጉዳይ የሚያነሱትም ስለማይመለከታቸው ሃሳብ የማንሳት መብት ቢኖራቸውም አያገባችሁም ብሎ መልስ መስጠት ብቻ ነው ሲሉ ዶክተር ደብረጺዮን ተናግረዋል።
የወልቃይት ነዋሪዎችን በተደጋጋሚ ችግር አለ ወይ?ብለን ጠይቀናቸው የለብንም ብለውናል ሲሉም ተናግረዋል።
ወልቃይቶች ጎንደሮችን አስታግሱልን እያሉን ነው ሲሉም ነው የተናገሩት።
ጎንደሮች የሚያነሱት ኋላ ቀር አመለካከት ነው ያሉት ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ይህንን የሚያስታግስ መንግስት አለመኖሩ ትልቅ ችግር ነውም ብለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የወልቃይት ጠገዴ የማንነት ከሚቴ አባላት በአዲስ መልክ መዋቀሩ ተነግሯል።
ይህ ኮሚቴ ወልቃይትን በተመለከተ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቢያቀርብም አዲሷ የምክር ቤቱ አፈጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ጉዳዩ የሕዝብ ውክልና ባላቸው አካላት ስላልቀረበ ተቀባይነት የላቸውም ማለታቸውም ተዘግቧል።