በአሶሳ ከተማና አካባቢው ግጭት ተቀሰቀሰ

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 20/2010) በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ ከተማና አካባቢው ግጭት መቀስቀሱ ተሰማ።

የግጭቱ መንስኤ በውል ባይታወቅም ችግሩ ከማንነት ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል።

በግጭቱ ሰባት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ቁጥሩ ከዚህ በላይ ሊጨምር ይችላል ብለዋል የኢሳት ምንጮች ከስፍራው።

በክልሉ ማኦ ኮሞ ወረዳ በቶንጎ ከተማም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድን ለመደገፍ ሰልፍ በወጡ ሰዎች ላይ ፖሊስ በከፈተው ተኩስ ሁለት ሰዎች ተገድለዋል።

በቤንሻንጉል ጉምዝ አሶሳ ከተማ ከፍተኛ ግጭት ከተቀሰቀሰ በኋላ በከተማዋ እንደገና ጸጥታ መስፈኑ ይነገራል።

የከተማዋ ነዋሪዎች ከቤታቸው እንዳይወጡ ስለተነገራቸው አካባቢው ጸጥ ረጭ ማለቱም ነው የተነገረው።

በከተማዋ የበርታ ተወላጆች በሌሎች ብሔሮች ላይ ተቃውሞ በማሰማት በተወሰኑት ላይም ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ታውቋል።

እስካሁን ከሆስፒታል የተገኙት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት 7 ሰዎች ተገድለዋል።የሟቾቹ ቁጥርም ከዚህ በላይ ሊጨመር እንደሚችል የሆስፒታሉ ባለሙያዎች ለኢሳት ተናግረዋል።

በአካባቢው የሚገኙት የኢሳት ምንጮች እንዳሉት ከሆነ ሰዎቹ የተገደሉት በተተኮሰባቸው ጥይት ነው።

የከተማዋ የፖሊስ ሃይል ሰልፈኞቹን ተገን በማድረግ በሕዝቡ ላይ ተኩስ በመክፈቱ ለበርካቶች ሕይወት መጥፋትና ለከፋ ጉዳት መዳረጉን ምንጮቹ ጨምረው ገልጸዋል።

የአሶሳ ከተማ ተረጋግታለች ቢባልም አሁንም ግን የጥይት ተኩስ አልፎ አልፎ እየተሰማ መሆኑንና ግጭቱን ለመከላከልም የመከላከያና የጸጥታ ሃይሎች በአካባቢው መሰማራታቸውን የኢሳት ምንጮች ተናግረዋል።

የከተማዋ ነዋሪም የሚደርስበትን ጥቃት ለመከላከል ዝግጁ ሆኖ በመጠባበቅ ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በቤንሻንጉል ጉምዝ ማኦ ኮሞ ወረዳ ቶንጎ ከተማ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ድጋፍ በወጡ ሰዎች ላይ ተኩስ ተከፍቶ ሁለት ሰዎች ተገድለዋል።

ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ሁለቱን ሰዎች የገደሉት የክልሉ ልዩ ፖሊስ አባላት ናቸው።

በጥቃቱ 40 ሌሎች ሰዎች መቁሰላቸውም ተነግሯል።

በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በተለይም በአማራና ኦሮሞ ተወላጆች ላይ ጥቃት እየተሰነዘረ እንደሆነ ይነገራል።

በአካባቢው ያሉ በርታዎች  አሁን ባለው የኢሕአዴግ አስተዳደር በርካታ ቅሬታዎችን ሲያቀርቡ መቆየታቸውም ይታወሳል።

በክልሉ የጉምዝና ሌሎች ብሔረሰቦችም የመልካም አስተዳደርና በአካባቢው የተፈጥሮ ሃብት ተጠቃሚዎች አይደለንም ሲሉ ቆይተዋል።