በተለያዩ አካባቢዎች ግጭት ለማስነሳት ትንኮሳ የሚያደርጉ ሃይሎች እና ጠ/ሚኒስትሩን ለመግደል የሞከሩ ሃይሎች አንድ መሆናቸውን መንግስት አስታወቀ

በተለያዩ አካባቢዎች ግጭት ለማስነሳት ትንኮሳ የሚያደርጉ ሃይሎች እና ጠ/ሚኒስትሩን ለመግደል የሞከሩ ሃይሎች አንድ መሆናቸውን መንግስት አስታወቀ
(ኢሳት ዜና ሰኔ 20 ቀን 2010 ዓ/ም) ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ላይ በህዝቡ ላይ ጥቃት ለማድረስ የሞከሩ ሃይሎች በተለያዩ ቦታዎች የትንኮሳ ድርጊቶችን ሊፈጽሙ እንደሚችሉና ጥንቃቄ እንዲደረግ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት አስታውቋል።
እነዚህ ሃይሎች በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ትንኮሳዎችን ይፈጽማሉ የሚል ጥርጣሬ በመኖሩ ህዝቡ ከወትሮው በተለየ መልኩ ጥንቃቄ ማድረግና ከጸጥታ ሃይሎች ጋር ተቀራርቦ መስራት እንደሚያስፈልግ የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ገልጸዋል።
ህዝብ በሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች፣ የአገር መሪዎችና ከፍተኛ ባለስልጣናት በሚንቀሳቀሱበት፣ ትላልቅ የመሰረት ልማት ፕሮጅክቶችና ፋብሪካዎች አካባቢ ጥንቃቄ እንዲደረግና ህዝብ በንቃት እንዲከታተል ጥሪ አቅርበዋል።
ህዝብን ከህዝብ የማጋጨት አንድነትን የሚሸረሽር ስራዎች ሊኖሩ እንደሚችሉም ተገልጿል።
በተለያዩ አካባቢዎች ሲከሰቱ የነበሩ ብሄርን ማእከል ያደረጉ ግጭቶች እንዲሁም የግድያ ሙከራዎች በአንድ አካል የሚፈጸሙ መሆናቸውን መንግስት ሲገልጽ ይህ የመጀመሪያ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በደቡብ ክልል የተነሱ ግጭቶችን ተከትሎ የደኢህዴን ሊ/መንበርና ምክትል ሊ/መንበር ከስልጣን ወረደዋል። የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ደሴ ዳልኬም ስልጣናቸውን ይለቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።