(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 12/2010)የብሄራዊ ባንክ ገዢ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ ከሥልጣን ተነሱ
በምትካቸው የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽነሩ ዶክተር ይናገር ደሴ ተሹመዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ በቃሉ ዘለቀ ደግሞ ምክትል ፕሬዝዳንት እንደሚሆኑ ተመልክቷል።
አንዳንድ የዘርፉ ባለሙያዎች ሹመቱ ያልተጠበቀ እና ከሙያው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ለሌላቸው የተሰጠ ሲሉ ተችተዋል።
ከ10 ዓመታት በላይ በብሄራዊ ባንክ ገዢነት የቆዩትና አሁን ከሃላፊነት የተነሱት አቶ ተክለወልድ አጥናፉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ አማካሪ ሆነው መሾማቸውም ተዘግቧል።
ትናንት ሰኔ 11/2010 የብሄራዊ ባንክ ገዢ ሆነው የተሾሙት ዶ/ር ይናገር ደሴ የብሄራዊ ፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆን ያገለገሉ ሲሆን፣ቀደም ሲልም በተለያዩ ሃላፊነቶች ማገልገላቸው ተመልክቷል።
ዶክተር ይናገር ደሴ በሙያቸው ኢኮኖሚስት ቢሆኑም ፣ትምህርታቸው እንዲሁም ልምዳቸው ለተሰጣቸው ስልጣን የማያበቃቸው መሆኑን አንዳንድ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።
ዶክተር ይናገር ደሴ በሙያቸው ኢንቫሮመንታል ኢኮኖሚስት ሲሆኑ፣ለብሔራዊ ባንክ ገዢነት የሚያስፈልገው ዘርፍ ማክሮ ኢኮኖሚስት እንደሆንም ተመልክቷል።
ምክትል ገዢ ሆነው መሾማቸው የሚጠቀሰው አቶ በቃሉ ዘለቀ ለረዥም አመታት የኢትዮጵ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት ሆነው አገልግለዋል።
እሳቸውም በሙያቸው አካውንታንት በመሆናቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ዕውቀት በሚፈልገው ተቋም በምክትል ገዢነት መሾማቸውንም ባለሙያዎቹ ተችተዋል።አቶ በቃሉ ዘለቀ የንግድ ባንክ የቦርድ ሊቀመንበር ከነበሩት አቶ አባይ ጸሃዬ ጋር በመሆን በንግድ ባንክ ላይ ባደረሱት ጉዳት ሊጠየቁ ሲገባቸው ወደ ሌላ ሥፍራ እንዲዛወሩ ማድረግም ተገቢ አለመሆኑን የባንክ ምንጮች ገልጸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከፓርቲ አባላት ባሻገር ሄደው ባለሙያዎችን መፈልግ እና መሾም እንደሚገባቸው የሚያሳስቡት ባለሙያዎች በዚህ ረገድ የተደረገውንም ጥረት አስታውሰዋል።
በዓላም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ውስጥ የሚሰሩትን አቶ አበበ አዕምሮሥላሴን ለመሾም ጠይቀው እንዳልተሳካላቸው መዘገባችን ይታወሳል ።
በሃገር ውስጥም ብቁ የመስኩ ባለሙያዎች እያሉ ሹመቱ በፓርቲ መዋቅር ላይ መመርኮዝ እንዳልነበረበትም ተገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት እንዳስታወቀው ከ10 ዓመታት በላይ በብሄራዊ ባንክ ገዢነት የቆዩትና አሁን ከሃላፊነት የተነሱት አቶ ተክለወልድ አጥናፉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፋይናንስ አማካሪ ሆነው ተሹመዋል።