ጠ/ሚ አብይ አህመድ ግልጽነት የተሞባለትና በብዙዎች የተወደሱበትን የመጀመሪያ ሪፖርት አቀረቡ
(ኢሳት ዜና ሰኔ 11 ቀን 2010 ዓ/ም) ዶ/ር አብይ አህመድ ዛሬ ከፓርላማ አባላት ለተነሱ በርካታ ጥያቄዎች መልስ የሰጡ ሲሆን፣ ትንተናዎቻቸውና ገልጽነታቸው ንግግሩን በስሜት ያዳምጡ በነበሩ የማህበራዊ ሚዲያ ታዳሚዎች ዘንድ ተቀባይነት አግኝተዋል። ዶ/ር አብይ ከዚህ በፊት የነበሩ ሁለት ጠ/ሚኒስትሮች ያደርጉ እንደነበረው ከፓርላማ ወንበራቸው ላይ ሆነው ሳይሆን፣ ሚኒስትሮችና የመምሪያ ሃላፊዎች መልስ ሲሰጡ ከሚቀመጡበት አፈጉባኤዋ ጎን ተቀምጠው መልስ መስጠታቸው የ26 አመታትን የፓርላማ ባህል ለመቀየር የታሰበ በጎ ጀምር ተደርጎ ተወስዷል።
በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መንግስታቸው ያከናወናቸውን ጉዳዮች ሪፖርት ያቀረቡት ጠ/ሚኒስትር አብይ፣ ከሪፖርታቸው በሁዋላ የተለያዩ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል።
መንግስት የልማት ድርጅቶችን ለመሸጥ የወሰነባቸውን ምክንያቶች በዝርዝር የገለጹት ጠ/ሚኒስትሩ አንዱ ምክንያት ባላፉት ጊዜያት አገሪቱ ከፍተኛ ብድር በመውሰዱዋና የመክፈያ ጊዜው በመቃረቡ መሆኑን ገልጸዋል። ቀድም ብለው የተገነበሩት መሰረተ ልማቶች ጥራት በሌላቸው እቃዎች መገንባታቸውን ፣ ሙስናና አድሎ የተፈጸመባቸው መሆኑን የገለጹት ዶ/ር አብይ አሁን ደግሞ የኢኮኖሚ አሻጥር እየተፈጸመ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ በፊት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ሲሸጡ በጥቂት ሰዎች እንዲያዝ መደረጉ ትክክል አለመሆኑን በተለይ የማእድን ሽያጭ ለአንድ ግለሰብ መሸጥ እንዳልነበረበትና ህብረተሰቡ ቢያንስ ከ10 እስከ 15 በመቶ ሊገዛ ይገባው እንደነበርና ይህንንም ለመቀየር መንግስት ማሰቡን ተናግረዋል። የቡና እርሻዎችም በተመሳሳይ መንገድ መሸጣቸው አግባብ እንዳልነበር ገልጸዋል።
አሁንም ቴሌ፣ መብራት ሃይልና አየር መንገድ የመሳሰሉ ድርጅቶች ሲሸጡ 5 በመቶ ለኢትዮጵያውያን እንደሚከፋፈል፣ አንድ ግለሰብ ብቻውን 5 በመቶ የሚሆነውን አክሲዮን መግዛት እንደማይፈቀድለት፣ ከ30-40 በመቶ የሚሆነውን ደግሞ በሙያው ከፍተኛ ልምድ ላላቻው ኩባንያዎች እንደሚሰጥ፣ ዋናው አክሲዮን ግን በመንግስት እጅ እንደሚቆይ ዶ/ር አብይ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ሲደወሉ የኢትዮጵያ ቁጥር የሚወጣው አጭበርባሪዎች ስልኩን ስለሚጠልፉትና ለራሳቸው የሃብት መሰብሰቢያ ስለሚያውሉት ነው ብለዋል። ቴሌ ከውጭ በዶላር የሚያገኘው ገንዘብ አነስተኛ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።
ቴሌ እቃ በመግዛት የሚያድግ የሚመስለው መስሪያ ቤት ነው ያሉት ዶ/ር አብይ፣ ከፍተኛ የሃብት ብክንት የሚታይበት፣ በየቦታው አጥሮ የያዛቸውን ቦታዎችም ወደ መንግስት ለማዞር እቅድ መኖሩን ተናግረዋል።
ዶ/ር አብይ የፌደራል ስርአቱን በተመለከተ የሃሳብ መንሻፈፍ አለ ብለዋል።
ድንበርና ወሰን መምታት የፈጠረው ችግር እንዳለ የሚናገሩት ጠ/ሚኒስትሩ፣ አንድ ኢትዮጵያውያዊ ጅግጅጋ ካልኖረ፣ ወላይታ ሲዳማ ውስጥ መኖር ካልቻለ ፣ በግብጽ፣ ሱዳንና ደቡብ አፍሪካ በኢትዮጵያውያን የሚወሰደው እርምጃ ትክክል ነበር ማለት ነውን? ሲሉ የጠየቁት ዶ/ር አብይ፣ ፌደራሊዝም ትላልቅ ግጭቶችን እንጅ ትናንሽ ግጭቶችን የሚፈታ አይደለም ብለዋል። ህዝቡ ድንበርን በተመለከተ ያለው አመለካከት ሊቀየር እንደሚገባ ፣ ከሁሉም በላይ የቅኝ ግዛት ድንበሮች አንድን ማህበረሰብ ለሁለት መክፈላቸውን በመጥቀስ ህዝቡ ከዚህ ባለፈ ማየት እንደሚገባው መክረዋል።
በቅርቡ ህወሃት የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ያወጣውን መግለጫ በመቃወም ላወጣው መግለጫ ተዘዋዋሪ መንገድ መልስ የሰጡት ዶ/ር አብይ፣ በመጀመሪያ ውሳኔው ስለባድመ ሳይሆን በአጠቃላይ ስላለው 1 ሺ ኬ/ሜ ስለሚደርስ የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር መሆኑን፣ ለኢህአዴግ የምክር ቤት አባላት አለማወያየታቸውን ነገር ግን ስራ አስፈጻሚው ከወሰነ በሁዋላ አባሎቻቸው ህዝቡን ሂደው እንዲያወያዩ ፍላጎታቸው እንደነበር ተናግረዋል።
“ድብቅ ፖለቲካ ከእንግዲህ አይሰራም፣ እኛ ሸርበንና ደብቀን የምናስተላልፈው ውሳኔ የለም”፣ ያሉት ዶ/ር አብይ ፣ ለፖለቲካ ፍጆታ ተብሎ በሚስጢር እንደተወሰነ የሚቀርበው ትክክል አለመሆኑን ገልጸዋል።
“አሰብን ስንሰጥ መቼ ህዝብ አወያይተናል? አስብ ላይ የሞተውም እኮ ኢትዮጵያዊ ነው” በማለት ሲናገሩ አንዳንድ የፓርላማ አባላት አፋቸውን ሲይዙ ተይተዋል። የባድመ ውጊያ ይቁም ሲባል ማልቀሳቸውን የገለጹት ዶ/ር አብይ፣ በጦርነቱ ወንድማቸውንና ጓደኞቻቸውን እንደቀበሩ ተናግረዋል።
ለፓርላማ አባላቱ ደግሞ እናንተ የወሰናችሁት ነው የምናስፈጽመው በማለት ፓርላመው በውሳኔው እጁ እንዳለበት ገልጸዋል
ዶ/ር አብይ አሸባሪ ማለት ስልጣን ይዞ ስልጣኑን ለማቆየት ህገመንግስትን በመጣስ የሃይል እርምጃ የሚወስድ እንዲሁም ስልጣን ለመያዝ ሃይል የሚጠቀም ነው ያሉት ዶ/ር አብይ፣ ህገ መንግስቱ መከላከያውና ደህንነቱ ከፖለቲካ ፓርቲ ገለልተኛ ቢልም በእኛ አገር ግን ያለው እውነታ ሌላ ነው ፣ በእኛ ሁኔታ ከክልል እስከ ወረዳ እስረኞችን አስሮ ጨለማ ቤት መክተት፣ ማሰቃየት ሁሉ ሽብርተኝነት ነው ብለዋል።
መንግስት ስልጣኑን ለማቆየተ የሽብር ተግባር መፈጸሙንና ህዝቡን ይቅርታ መጠየቁን የገለጹት ዶ/ር አብይ፣ ግንቦት7፣ ኦብነግና ኦነግም ስልጣን ለመያዝ የሚጠቀሙበትን የሃይል አማራጭ እንዲተው፣ ከእንግዲህ ዶ/ር ብርሃኑን ገድዬ ስልጣን መያዝ፣ ዶ/ር ብርሃኑም እኔን ገድሎ ስልጣን ለመያዝ መሞከር ጊዜው ያለፈበት አስተሳሰብ” ብለዋል። ለኢትዮጵያ እኛ ብቻ አይደለም የምንቆረቆረው፣ ሁሉም ይቆረቆራል በማለት የሃይል አማራጭ የሚጠቀሙ ተቃዋሚዎችም ለአገራቸው እንደሚቆረቆሩና በመልካም አይን መታየት እንዳለበታቸው ገልጸዋል። የእኛ ድርሻ የፖለቲካ ሜዳውን ማስፋት ነው የሚሉት ዶ/ር አብይ፣ ኤራትራ ያሉ ተቃዋሚዎች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ጠይቀወዋል።
ሙስና ፈጽመዋል በተባሉት ላይ እርምጃ ሲወሰድ ቢቆይም ፣ ሙስና በሁሉም ክልል ከላይ እስከታች ተስፋፈቶ ባህል ሆኗል ያሉት ጠ/ሚ አብይ፣ ምክንያቶቹ ደግሞ ዋናውን ትቶ ቅርንጫፍ ላይ ትኩረት በመደረጉ፣ የዲሞክራሲ አለመስፋፋተና የህግ አውጭው፣ ህግ ተርጓሚውና የስራ አስፈጻሚው እርስ በርስ መቆጣጠር አለመቻል እንዲሁም የፍትህ እጦት መሆኑን አስረድተዋል።
ሌቦች ሰርቀው እንኳን አርፈው አይቀመጡም፣ አሁንም እየዶለቱ ነው በማለት የገለጹት ዶ/ር አብይ፣ ያም ሆኖ እንደ ከዚህ ቀደሙ አስረን ማስረጃ ከምንፈልግ፣ ማስረጃ ፈልገን ማሰርን እንመርጣለን ብለዋል።
ዶ/ር አብይ ሚዲያው ነጻ መሆን እንዳለበት፣ በደህንነትና በመከላከያው የተጀመረው ለውጥ መቀጠል እንደሚገባው እንዲሁም የሽብርተኝነት አዋጁ መፈተሽ እንዳለበትም ተናግረዋል። የፍትህ ስርዓቱ ከበደንና ተሰማን እኩል የማያይ በመሆኑ መሻሻል እንደሚደረገብትም ተናግረዋል።
“ህወሃት ማለት የትግራይ ህዝብ አይደለም” በማለት ህወሃትና የትግራይን ህዝብ መለየት እንደሚገባ የተናገሩት ዶ/ር አብይ፣ ጥቂቶች በስሙ ነገደው ይሆናል፣ ህዝቡ ግን በስሙ ያገኘው ነገር የለም ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን በዶ/ር አብይ ንግግር ላይ የተለያዩ አስተያየቶችን ሰጥዋል። በቅርቡ የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ ሊ/መንበር ሆነው የተመረጡት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ፣ “ አብይ አህመድ የሚያስበውን ነገር ፊት ለፊት መናገሩ : በድፍረት አካፋን አካፋ ማለቱ : የህወሃትን ነውሮች እየነቀሰ በድፍረት አባላቱን መገሰጡና በርቱዕ
አንደበቱ አቁዋሙን ያብራራበት መንገድ ክስተት ነው::” ሲሉ፣ ጋዜጠኛ በላይ ማናየ ደግሞ “የዛሬው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የፓርላማ ንግግር በአጭሩ ላለፉት 27 አመታት የሄድንበት መንገድ ምን ያህል አስቀያሚ እና አደገኛ እንደነበር በለውጥ ፈላጊ እና አስተዋይ ኢትዮጵያውያን ሲነገር ቆይቶ ሰሚ አጥቶ የነበር ጉዳይ በጠ/ሚ አብይ አንደበት ጠቅለል ተደርጎ የተነገረበት መሆኑ ነው። አብይ አህመድ ጠ/ሚ ሆኖ ይህን ሲናገር፣ መለስ ዜናዊ በህይወት ኖሮ ቢሰማ እንዴት የሞት ሞት በሞተ ነበር!” ብሎአል።
ገመቹ መረራ ፋና የተባለ ጸሃፊ ደግሞ “«ሕገ መንግሥቱን በፓርላማው ፊት በንግግር ለመናድ ሲሞክር እጅ ከፍንጅ ተይዟል» ብለው አይከሱትም አይደል?” ሲል የጠየቀ ሲሆን፣ ሰለሞን ስዩም ደግሞ “ጠ/ሚሩ ብዙ ጉዳዮች ላይ ” አንቺው ታመጪው፣ አንቺው ታሮጪው” በሚል ዘይቤ ጥያቄውን መልሶ ለወያኔ ወርውሮላቸዋል። ሶፊስቱ_ አፈጮሌው መለስ ዜናዊን ደግሞ ባይገድለውም፣ ደህና አድርጎ ቀብሮታል።” ሲል አስተያየቱን አስፍሯል።