ህወሃት- የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ በባድመና የመንግስት ኢኮኖሚ ተቋማት ዙሪያ የወሰናቸውን ውሳኔዎች እንደሚቀበል አስታወቀ
(ኢሳት ዜና ሰኔ 7 ቀን 2010 ዓ/ም) በቅርቡ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባድመን ለኤርትራ የወሰነውን የአልጀርሱን ስምምነት እንደሚቀበል እንዲሁም ዋና ዋና የሚባሉትን የመንግስት የልማት ድርጅቶችን በከፊል ወይም በሙሉ ወደ ግል ለማዞር የወሰነውን ውሳኔ የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ እንደሚቀበለው ሲያስታውቅ፣ አፈጻጸሙ ላይ ግን ጥንቃቄ ይደረግ ብሎአል።
ህወሃት ትናንት ባወጣው መግለጫ፣ “የኢህኣዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያሳለፈዉ ዉሳኔ በመሰረቱ ከሰላም ፖሊስያችን ጋር የተጣጣመ መሆኑን በማረጋገጥ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚያስችል ዉሳኔ መተላለፉ ተገቢና ዉቅታዊ መሆኑን የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ደምድሟል።” ብሎአል።
ህወሃት አክሎም “የኢህኣዴግ ስራ ኣሰፈፃሚ ኮሚቴ አሁን ከመንግስት የልማት ድርጅቶች መካከል ቴሌ፣ ኤለክትሪክ ማመንጨዎች፣ ሎጀስቲክስና የኢትዮዽያ ኣየር መንገድ ከፍተኛዉ ድርሻ በመያዝ የግል ባለሃበቶችን ለማሳተፍ እንዲሁም የቀሩትን የልማት ድርጅቶች በከፊል ወይም በሙሉ ወደ ግል ይዞታ ለማስተላለፍ የወሰነዉ ውሳኔ ከፕሮግራማችንና ፖሊስዎቻችን ጋር የማይጋጭ፣ ባለፉት ጉባኤዎቻችን እየተወሰነ የመጣና ወቅታዊ መሆኑን በማረጋገጥ ተቀብሎታል።” ሲል ሁለቱንም ውሳኔዎች መቀበሉን አስታውቋል።
ህወሃት ከእነዚህ ውሳኔዎች በፊት መቅደም ነበረባቸው በማለት የኢህአዴግን ስራ አስፈጻሚ ውሳኔ የሚተቹ አስተያየቶችንም አቅርቧል። ከሁሉ በፊት መሰረታዊ የአመራር ብልሽትና ያስከተለው ጉዳት ሊገመገም ይገባ ነበር ብሏል-ህወሃት።የድንበር ማካለል ኣፈፃፀሙን በሚመለከት ግን ሃገራችን ከሌሎች ጎረቤት ሃገራት ጋር ከሏት የአዋሳኝ ድንበር ጉዳዮች አንፃር ጭምር እጅግ ከፍ ያለ ትርጉም ያለዉ በመሆኑ፣ በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊታይ ይገበዋል ብሎአል።
ህወሃት “በኢትዮ-ኤርትራ ዘላቂ ሰላም ጉዳይም ሆነ ከመንግስት የልማት ድርጅቶች ጋር በተያየዘ የተወሰኑ ውሳኔዎች ወደ ኢህአዴግ ምክርቤት ሳይቀርቡ፣ አጋር ድርጅቶች ሳይሳተፉበት እና የሚመልከታቸው አካላት በዝርዝር ሳይወያዩበት እንደመጨረሻ ውሳኔ ተወስዶ ለህዝብ ይፋ መደረጉ አንድ ጉድለት ነው” ሲል ተችቷል። የኢትዮዽያ ብሔር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ከዳር እስከዳር በከፍተኛ ሃገር ፍቅር የተሳተፉበት እና መስዋእት የከፈሉበት ጉዳይ በዝርዝር ሳይወያዩበት እና በቂ መተማመን ሳይደረስበት በሚድያ ይፋ መግለጫ መሰጠቱ፣ ህዝባችን ላይ ቅሬታ፣ ቁጣና መደነጋገር የፈጠረ መሆኑም-የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ውሳኔ ሌላው ድክመት ነው ሲል አክሏል።
“በኢህአዴግ ደረጃ እየተደረጉ ያሉ የኢህአዴግን ህገ-ደንብ እና ተቋማዊ አስራር ያልተከተሉ የአመራር ምዳባዎች እንዲታረሙ” የሚለው የህወኃት መግለጫ፣ ለደርጅታችን ነባር አመራሮች እውቅና እንዲሰጥ ሲልም ጠይቋል።
ህወሃት ከማንነት ጋር በተያያዙ የትግራይን ህዝብ አንድነትና ሰላም ለመረበሽ እየተደረጉ ናቸው ያላቸውን አደጋዎች በጽናት እንደሚታገላቸው በመጥቀስ፣ የትግራይን ህዝብ ለማዳከም እና ለመምታት በተለያዩ መንገዶች ፀረ ትግራይ ህዝብ እና ፀረ ህወሓት እንቅስቃሴ የሚያድርጉ የውስጥም የውጭም ሓይሎችን ህዝቡ ኣምሮ እንዲታግላቸው ሲል ጥሪውን አቅርቧል።
ወቅታዊ ሁኔታዉን በፍጥነት ለማየት እና ለመገምገም የኢህኣዴግ ስራ አስፈፃሚ እና ምክርቤት አስቸኳይ ሰብሰባ እንዲጠራም የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ጠይቋል።
በህዋሀት መግለጫ ዙሪያ ከአምቦ ዩኒቨርስቲ መምህር ስዩም ተሾመ እንዲሁም በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም አስተባባሪና በራያ የማንነት ጥያቄና በሰብአዊ መብቶች መከበር ዙሪያ ትግል ከሚያደርጉት ከአቶ አግዘው ህዳሩ ጋር ያደረግነውን ውይይት በልዩ ዝግጅት ይዘን እንቀርባለን።